ባሕር ዳር፡ ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የጥርን በባሕር ዳር መርሐ ግብር አካል የኾነውን የጀልባ ሽርሽር አካሄዷል።
በባሕላዊ ሙዚቃ እና ትዕይንት በታጀበው በዚህ የጀልባ ሽርሽር በከተማ አሥተዳደሩ የሚገኙ እና በተለያዩ ሥራ ዘርፎች የተሰማሩ የድርጅት ባለቤቶች እና ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው በጥር ወር ባሕር ዳርን ፈልገው የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ጀልባዎችን እና ወደቦችን መርጠው እንዲጎበኙ የታለመ የጀልባ ሽርሽር መካሄዱን ተናግረዋል።
ጉብኝቱ የከተማችን ምልክት በመኾን በተያዘው 2018 የትራንስፖርት አገልግሎት የጀመረችው ጣናነሽ ቁጥር ሁለትን ያካተተ ነው ብለዋል።
ባሕር ዳር ለቱሪዝም የተሰጠች ብዙ ጸጋዎች ያሏት ከተማ ናት ያሉት ኀላፊው ይህን ጸጋዋን ጎብኝዎች እንዲጎበኙ ጥርን በባሕር ዳር የተቀናጀ ፌስቲቫል እየተከናወነ መኾኑን ጠቅሰዋል። የጥርን በባሕር ዳር ፌስቲቫል አሁንም እስከ ጥር 30 ይቀጥላል ነው ያሉት።
የባሕር ዳር መገለጫ የኾነው የታንኳ ውድድር በሁለቱም ጾታ ይከናወናል፤ በድምቀት የሚከበረው የሰባር አፅሙ ጊዮርጊስ ሃይማኖታዊ በዓል እና ሌሎች ፌስቲቫሎች በጉጉት ይጠበቃሉ ብለዋል።
አሁን ላይ በከተማችን በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ከትመዋል ያሉት ኀላፊው ቀጣይም በርካታ እንግዶች ወደ ከተማዋ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ከተማዋን የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጡ እና የከተማዋ ነዋሪ የተለመደውን የእንግዳ አቀባበል እንዲያደርግ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጀልባ ሽርሽሩ ተሳታፊ አርቲስት ታደሰ ላቀው በጀልባ ሽርሽሩ መደሰታቸውን ነግረውናል። ጥርን በባሕር ዳር ፌስቲቫል ባሕር ዳርን የበለጠ ያጎላታል ብለዋል።
ባሕር ዳር አድናቂዎቿ ብዙ ናቸው፤ ጎብኝዎች እንደፈለገ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ጎብኝተው ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ ግን ሰላም ያስፈልጋል፤ አሁን ላይ ያለውን ኹኔታ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ሌላኛዋ በስጦታ እቃዎች ሽያጭ የተሠማራችው የጀልባ ሽርሽሩ ተሳታፊ ኢየሩስ ጀንበሬ ከዚህ በፊት በእንደዚህ አይነት ኹነት ተሳትፋ እንደማታውቅ ነግራናለች። በዛሬው የጀልባ ሽርሽር መደሰቷንም ጠቅሳለች።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ባሕር ዳር መጥተው ጥርን በባሕር ዳር እንዲያሳልፋም መልዕክት አስተላልፋለች።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን









