ከግሽ ተራራ ግርጌ አቡነ ዘርዓብሩክ ታዛ ስር!

0
40
ባሕር ዳር: ጥር 13/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ታናናሾቹ በራሪ ወረቀቶች ብዙ ብለውለታል። የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚም በሉት የማኅበራዊ የስበት ማዕከል ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል ዓባይ።
የዓለማችን ባለግርማ እና ከሰከላ እስከ ሜዲትራኒያን ባሕር የተዘረጋ ለዕልፍ ነፍሳት መቆያም ኾኖ አገልግሏል።
ገነትን ከሚያጠጡ አራቱ አፍላጋት አንዱ የኾነው ዓባይ መነሻው ሰከላ ነው። ይህ ስፍራ እንዲከበር እና እንዲታይ ምክንያት የኾነው ደግሞ በአቡነ ዘርዓብሩክ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ የፈለቀው ጸበል ነበር።
ይህ ስፍራ ታላቁ የዓለማችን ወንዝ እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ በርካቶች ከህመማቸው የሚፈወሱበትም ኾኖ ዘመን ተሻግሯል።
የኢትዮጵያን ምድር የሚከብበው ዓባይ ካርቱም እና ካይሮ ወርዶ ሜዲትራኒያን ይዘልቃል። የዓለማችን ኃያላኑ መሪዎች የሚያማትሩበት ይህ ስፍራ ውልደቱ ከግሽ ተራራ ግርጌ ከአቡነ ዘርዓብሩክ ታዛ ነው።
ዓባይ የምሥራቅ አፍሪካን የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ መልክም የሚበይን፤ የዓለምን የኃይል አሰላለፍ የሚወስን ግዙፍ ብሎም ቀዳሚ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያውያን የችግራቸው መፍቻ ቁልፍ የተቋጠረበት ዓባይ ቅኔ ነው። የትናንት ታሪካችን፣ የዛሬ ማንነታችን እና የነገ ዕጣ ፈንታችንም ነው።
መጭውን ጊዜ ስናስብም የኢትዮጵያውያን ዕጣ የሚወሰነው በዚሁ ስፍራ ነው። በዓባይ ላይ የሚኖረን አረዳድ ለአሁኗ ኢትዮጵያ መጎስቆልም ኾነ መመንደግ ወሳኝ ነው።
የግዮን በዓል በሰከላዋ ግሽ ተራራ ግርጌ የሚከበረውም ያለምክንያት አይደለም፤ የግዮን በዓል የአንድነት፣ የትብብር እና የኢትዮጵያዊነት በዓል በመኾኑ እንጅ።
የግዮን አሊያም የአቡነ ዘርዓ ብሩክ በዓል የመግዘፍ፣ የመተለቅ፣ የመቻል እና ድል የማድረግም በዓል ነው።
ይህ በዓል ሩቅ እሳቤ ያለው በቅኝ ግዛት እሳቤ ላይ የቆሙ ያረጁ ስምምነቶችን ሁሉ በአዲስ የሚተካ፤ እኩልነትን፣ ትብብርን እና ወንድማማችነትን የማወጅ፤ የፍትሕ እና የአስተሳሰብ ርቀት የሚቀነቀንበትም ነው።
የዓባይ ወንዝ ግዝፈቱ እና መሠረቱ ገባሮቹን ማከሉ ከእነሱም ጋር ማበሩ እንደኾነው ሁሉ የኢትዮጵያውያንም ነጻነት እና ድል አድራጊነት የሚመነጨው ከአንድነት ነው።
የግዮን በዓል በጠባብ አዕምሮ ተራምደው የሠሩትን ዘረኛ ሥርዓት እና መዋቅር በመናድ በምትኩ በእኩልነት ላይ የሚገነባ አንድነትን እና ወንድማማችነትን የምንሰብክበት የኢትዮጵያዊነት አምሳያ እና መገለጫ ኾኖ የሚታይ ነው።
የግዮን በዓል በግሽ ተራራ ብቻ ሳይወሰን አስከ ቀይ ባሕር የዘለቀ የቀጣናውን ሀገራት ግንኙነት ከመሠረቱ በመለወጥ ትብብርን የሚያቀላጥፍ ዓለም ዓቀፋዊ ፋይዳ ያለው በዓል ኾኖ እንዲከበር ጥረትም እየተደረገ ነው።
በምሥጋናው ብርሃኔ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here