የዕድሜ ባለጸጋዋ ታንኳ ቀዛፊ!

0
29
ባሕር ዳር፡ ጥር 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከምትታወቅባቸው ልዩ መልኮች መካከል ባሕላዊ የደንገል ታንኳ አንዱ ነው። ታንኳ በጣና እና ዙሪያ ገባው አካባቢ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ደግሞ ባለውለታ፣ እንጀራ መቁረሻ፣ ዘመድ ወገን መጠየቂያ፣ የዘመናት ጌጣቸው ጭምር ነው።
የደብረ ማርያም ቀበሌ ኗሪ የኾኑት ወይዘሮ ጸሐይነሽ ጀምበርም በታንኳ ከ15 ዓመታቸው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በብዙ መገልገላቸውን ነግረውናል። አሁን ላይ የ55 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ ናቸው። በታዳጊነት ዕድሚያቸው እናት እና አባታቸውን በሞት ከተነጠቁ በኋላ ጨፌ እና እንጨት ወደ ባሕር ዳር ከተማ በታንኳ እያጓጓዙ ታናሽ እህት እና ወንድማቸውን አሳድገውበታል።
ታናናሾቻቸውን ለቁም ነገር ካደረሱ በኋላም ትዳር መሥርተው የራሳቸውን የሕይዎት ጉዞ ለማስቀጠልም ታንኳ ውለታውን በቃችሁ አላላቸውም። ሞት የትዳር አጋራቸውን እንደወላጆቻቸው ነጥቆ አንገት ሊያስደፋቸው ቢሞክሩም ለአንድ ልጃቸው ሲሉ ለሀዘን እና ለችግር እጅ ሳይሰጡ በባለውለታለው ታንኳ ኑሮን መክተዋል።
የልጅ ማሳደጊያ፤ የልጅ ማስተማሪያ፤ የወገን መጠየቂያ ባሕላዊ መጓጓዣቸው ኾኖ ዛሬ ድረስ ቀጥሏል። እርሳቸውም ታንኳ የዋለላቸውን ውለታ ሲገልጹ “ታንኳ ሕይዎት ነው” ነበር ያሉት።
ዕድሜ ሳይገታቸው ታላቁን የጣና ሐይቅ እና መካከሉን ገምሶ እንደሰጋር ፈረስ ጋልቦ በሚያልፈው የዓባይ ወንዝ ያለ ፍርሐት ፈጣሪያቸውን ተማምነው ለብዙ ዓመታት ከትንሿ ቀያቸው ደብረ ማርያም ወደ ውቧ ባሕር ዳር አጋምሰው ተመላልሰውበታል። ያውም ልጅ አዝለው፤ ያውም እቃ ጭነው፤ በቃ ታንኳ ለእርሳቸው ሁለ ነገራቸው ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ባሕር ዳር በፍሬዋ መልኳን ይበልጥ ልትገልጥ እና ጎብኝዎቿን በውበቷ ማርካ ልታስቀር በምታደርገው ጥርን በባሕር ዳር ፌስቲባል በተደጋጋሚ ተወዳድረዋል።
ጥርሴን በነቀልኩበት ማን እጅ ሊያስነሳኝ ብለው በታንኳ ቀዘፋ ውድድር ተወዳድረውም ለሁለት ዓመታት ከሴቶች አንደኛ እና ሁለተኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ ተሸልመዋል። በጨዋታችን መካከል ዘንድሮ ግን ትንሽ አመም አድርጎኝ አልተወዳደርኩም አሉኝ። አላስችል ብሎኝ ግን ልጀ ይወዳደር ስለነበር ለማየት ተገኝቸ ነበር ነው ያሉት።
ይህ ባሕላዊ የባሕር ዳር እና አካባቢው የትራንስፖርት ጌጥ፤ የዓባይ እና የጣና ጠያቂ ወዳጅ ተንኳ እና ቀዛፊ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገርም የበኩላቸውን እየተወጡ ይገኛሉ።
ልጄ አንድ ቢኾንም ገና በልጅነቱ ታንኳ መቅዘፍ አስለመጀዋለሁ ሲሉም አጫውተውኛል። ከባሕር ትራንስፖርት ውጭ ለቀያቸው አማራጭ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት አለመኖሩ የባሕላዊ መጓጓዣው ታንኳ ተጠቃሚ ሳይቀንስ እንደቀደመው ጊዜ ትውፊቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረጉንም ነግረውናል።
ለልጄ ታንኳ ቀዘፋ ማስለመዴ በቀያችን ትምህርት ቤት ስለሌለ በጣና ሐይቅ ላይ በታንኳ እየተመላለሰ ያለማንም እገዛ እንዲማር አግዞኛል ብለዋል። ወይዘሮ ፀሐይነሽ ውኃ ዋና ላይም የካበተ ልምድ እንዳላቸው ጠቅሰውልናል።
ታንኳ የማዘጋጀት ልምድ ግን የለኝም ብለዋል። አሁን ላይ እስከ 1 ሺህ 500 ብር ድረስ አንድ ታንኳ እየገዛሁ እገለገላለሁ ነው ያሉት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኅላፊ ጋሻው እንዳለው ደግሞ ታንኳን እንደ ብስክሌት ለከተማዋ መገለጫ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ነግረውናል። የጥርን በባሕር ዳር ፌስቲባሎች ውስጥ የባሕር ዳር አንዱ መለያ የኾነው የታንኳ ውድድር አንድ ማሳያ ነውም ብለዋል።
በዚህ ፌስቲቫል የተወዳዳሪዎች እና የተመልካቾች ቁጥር በየ ዓመቱ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መምጣቱንም አንስተዋል። ታንኳ የመቅዘፍ ፍላጎት ያላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎበኝዎች ቁጥርም ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል።
ለታንኳ ቀዛፊዎች በዓመት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ የሚደርስ ሥልጠና እንዲያገኙ መደረጉም ለዘርፋ ትኩረት እንደተሰጠው ማሳያ ነው ብለዋል። ታንኳ ቀዛፊዎች በማኅበር እንዲደራጁ ማድረግ እና ባሕላዊ ታንኳዎችን የማዘመን ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውንም ጠቅሰዋል።
በቀጣይም እንዲህ ዓይነት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፤ ሌሎች ሥራዎችም ይኖራሉ ነው ያሉት።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here