ደብረ ታቦር: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር የሚከበረውን የቅዱስ መርቆሬዎስ የንግሥ በዓል አስመልክቶ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቷል።
የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ደሴ መኮነን አውደ ርዕዩ የደበረ ታቦርን ባሕል እና እሴት ሊያሳይ በሚችል መንገድ የተዘጋጀ መኾኑን ገልጸዋል። ዝግጅቱ እስከ ቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ማጠናቀቂያ ድረስ እንደሚቆይም ተናግረዋል።
በየዓመቱ በድምቀት የሚከበረውን የቅዱስ መርቆሬዎስ በዓል ኑ በጋራ እናክብር ብለዋል በመልዕክታቸው።
“ባሕላዊ እሴቶች ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦቸው ከፈተኛ እንደኾነም” ተናግረዋል።
የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር አይቸው ዳውድ ከተማውን እና አካባቢውን ሊገልጽ የሚችል ታሪካዊ መለያዎችን ለአወደ ርዕዩ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ከአባቶች የተቀበሉትን ታሪክ ለትውልድ ለማስተላለፍ ባሕል እና እሴቶችን በማስጠበቅ በኩል ኀላፊነታቸውን እየተወጡ እንዳሉም ገልጸዋል።
የብርጋዴር ጄኔራል ኃይሌ መለስ የአንደኛ ደረጃ እና መካከለኛ ትምህርት ቤት መምህር ምጥን አልታሰብ የአከባቢውን ታሪክ በመከተብ እና በማዘጋጀት ለተማሪዎች የመረጃ መሣሪያ የሚኾን ቁሳቁሶችን በአውደ ርዕዩ ላይ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ያልተጻፈላቸው እና ያልተዘመረላቸው የእናቶች እና የአባቶቸን ድካም ለማስታወስ ያዘጋጁትን ባሕላዊ ቁሳቁስ ማሳየታቸውን ገልጸዋል።
በዝግጅቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የደብረ ታቦር ነዋሪዋ ወይዘሮ ኑሪት ዓለሙ በዓውደ ርዕዩ ላይ የተመለከቱት ታሪካዊ የፎቶ ኤግዚቪሽኖች እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









