ባሕር ዳር: የካቲት 05/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በጎንደር ዙሪያ ወረዳ ከማክሰኝት ከተማ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘዋ ደብረ ንግሥት አሯጌ ማርያም ቤተክርስቲያን የታሪክ፣ የእምነት እና የኪነ ሕንጻ ቅርስ በአንድ ላይ የተካተተባት ልዩ መዳረሻ ናት።
በአሯጌ ቀበሌ የምትገኝዋ ይህች ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ከክርስትና ታሪክ በላይ የአካባቢውን ባሕላዊ ውርስ የምትወክል ናት።
“አሯጌ” ተብላ ከመጠራቷ በፊት “እሩየ ማርያም” ትባል እንደነበር የቤተክርስቲያኗ አገልጋይ ቄስ ሰፈፈ ተገኘ ነግረውናል። “እሩየ” የሚለው ቃል ያማረ፣ የተዋበ እና ጥሩ ማለት መሆኑንም ገልጸውልናል። ቤተክርስቲያኗ ከስሟ ጀምሮ ውበትን እንደምታስተላልፍ ያሳያል ነው ያሉት።
በ17ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ሱስንዮስ ልጅ ልዕልት ወለተ ሐዋርያት እንደተመሠረተች የሚነገርላት አሯጌ ማርያም የመካከለኛው የጎንደር ዘመን የኪነ ሕንጻ ጥበብ አሻራ ያረፈባት ናት። ከኖራ፣ ከድንጋይ እና ከአካባቢው የተገኙ እፅዋትን በመጠቀም የተገነባችም ናት። አወቃቀሯ የጎንደር ዘመን ሕንጻ ባህሪን በግልፅ ያንጸባርቃል።
ቤተክርስቲያኗ በታሪክ ውስጥ ብዙ ፈተናዎችን ተጋፍጣለች። በ1881 ዓ.ም በደርቡሽ ወራሪዎች ተቃጥላለች። በ1933 ዓ.ም ደግሞ በጣሊያን ሠራዊት ከባድ መሣሪያ ጥቃት ተደርሶባታል። እነዚህ ጥቃቶች ታላቅ ጉዳት ቢያደርሱባትም መንፈሳዊ አገልግሎቷ አልቋረጠም።
በ1976 ዓ.ም ከመፍረሷ በኋላ ነባሩ መቅደስ በእንጨት በመሠራት አገልግሎቷ እንዲቀጥል ተደርጓል።
ውስጣዊ ቅርሶቿም ታሪካዊ እሴት ያላቸው ናቸው። የብራና መጻሕፍት፣ ጥንታዊ መስቀሎች፣ የልዕልት ወለተ ሐዋርያት የአልጋ ሸንኮር እና በወርቅ የተሰሩ የተለያዩ ዕቃዎች በቤተክርስቲያኗ ውስጥ እንዳሉ ተገልጿል። እነዚህ ቅርሶች ቤተክርስቲያኗን የታሪክ መዝገብ ያደርጓታል።
ከሁሉ በላይ የሚገርመው የቤተክርስቲያኗ ቅጥር ነው። አብዛኛው ክፍል ከሙሉ የአሠራር ጥበቡ እና ውበቱ ጋር 600 ዓመታትን ተሻግሮ እስከዛሬ ድረስ መድረሱ የቦታውን ታሪካዊ ክብር ያጎላዋል።
የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ በላይነህ መንግሥት እንደሚገልጹት ቤተክርስቲያኗን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የማስተዋወቅ እና የልማት ሥራዎች ተጀምረዋል።
በቋሚ ቅርስ ዝርዝር መዝገብ ውስጥ መመዝገቧ እንዲሁም በብሮሸር፣ በማኅበራዊ ሚዲያ እና በፎቶ እግዚቢሽን ማስተዋወቅ ሥራዎች መካሄዳቸው ተጠቅሷል።
ቢሆንም ቤተክርስቲያኗ በተፈጥሯዊ እና በሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት የደረሰባት መኾኑ ተገልጿል። የቅርስ ጥገና ሥራዎችን ማጠናከር እና የመንገድ መሠረተ ልማት ችግሮችን መፍታት እንደሚያስፈልግ ባለሙያው ይጠቁማሉ።
ይህ ከተፈጸመ ደብረ ንግሥት አሯጌ ማርያም በቱሪስቶች ዘንድ ተደራሽነቷን እየጨመረ የአካባቢውን ኢኮኖሚ ለማበረታታት እንደምትችል ይታመናል።
በዘመናት መካከል ተፈትና እንኳን የእምነት ብርሐኗ ያልጠፋችው አሯጌ ማርያም ዛሬም ከታሪክ ጋር በመቆም ለትውልድ የሚተርፍ ቅርስ መኾኗን ታስታውሳለች።
ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









