አረንጓዴ ሸማ የለበሰው የጥርባ ሐይቅ።

0
71
ባሕር ዳር: የካቲት 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥርባ ሐይቅ ከአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር ዋና ከተማ እንጅባራ ደቡብ ምሥራቃዊ አቅጣጫ ከምትገኘው ከአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ዋና ከተማ ግምጃ ቤት 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሦሥቱ ጥርባ ቀበሌ ይገኛል፡፡
ጥርባ ሐይቅ ተፈጥሯዊ ሐይቅ መኾኑን የአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ የሦስቱ ጥርባ ቀበሌ ነዋሪው አስር አለቃ አበበ ፀጋ ይናገራሉ።
ዙሪያውን በዕፀዋት የተከበበ መኾኑ እና በውስጡ የሚገኙ የአእዋፍ ዝማሬ አካባቢውን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸውልናል።
በዚሁ ድንቅ ስፍራ ኮማ፣ ሰሣ፣ ዝግባ እና ሌሎች ዛፎች እንደ ሚገኙበትም ያብራራሉ። የተለያዩ የዱር እንስሳት ማለትም እንደ ድኩላ፣ ነብር፣ ቀበሮ እና ሌሎችም እንሰሳት የሚገኙበት አካባቢ ነው።
ጥርባ ሐይቅ በዙሪያው የሚያጅቡት ዋሻዎች መኖራቸው ለቱሪስቶች ሁነኛ መዳረሻ አድርጎታልም ይላሉ።
በአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን ባለ ሙያ ከበደ ደመላሽ እንዳሉት ጥርባ ሐይቅ ከአዊ ብሄረሰብ አሥተዳደር ዋና ከተማ እንጅባራ ደቡብ ምሥራቃ አቅጣጫ ከምትገኘው ከአንከሻ ጓጉሳ ወረዳ ዋና ከተማ ግምጃ ቤት 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሦሥቱ ጥርባ ቀበሌ ይገኛል፡፡
የጥርባ ሐይቅ ለጥ ባለ ሜዳ አረንጓዴ ቀለምን ተላብሶ ከመኖሩ ባሻገር በዙሪያው የተፈጥሮ ደኖች ያስዋቡት ውብ ምድር በመኾኑ ቀልብን ይስባል ይላሉ፡፡
ሐይቁ የሰውን ቀልብ ከርቀት የሚስቡ የተለያዩ ዕድሜ ጠገብ የተፈጥሮ ደኖችን ጎረቤት አድርጎ ይገኛል። የተፈጥሮ ደኖቹ ለዱር እንስሳት መኖሪያ እና መጠለያ ኾነው ዓመታትን ተጉዘዋል።
ሐይቁ በዙሪያው ካሉ ደኖች ጋር ቤተሠብ ኾኖ ተጋምዶም ይኖራል። በነፋሻማ አየሩ የሰዎችን መንፈስ ከርቀት ይስባል። በውስጡም የተለያዩ የአዕዋፋት ዝርያዎች እና የዱር እንስሳት ይገኛሉም ነው ያሉት።
አረንጓዴ የለበሰ እና ልዩ ውበት ያለው ይህ የተፈጥሮ ስጦታ 25 ሄክታር መሬት ይሸፍል። 165 ሜትር ጥልቀትም አለው፡፡ ይህ ሐይቅ ከአካባቢው የተፈጥሮ ፀጋ ጋር ውህደት ፈጥሮ የተመልካችን ቀልብ በመግዛት ልዩ መግነጢሳዊ ኀይል የተላበሰ ስፍራም ነው።
በሐይቁ ቀረሶ፣ አንባዛ እና መሰል የዓሣ ዝርያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። ለጎብኝዎችም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ወለሊ ጌቴ ሐይቁን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የመንገድ መሠረተ ልማት እና ሌሎችም ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ብዋል። የቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚን ለማሳደግም እየተሠራ መኾኑን ነው የገለጹት።
ሐይቁን በማልማት በርካታ ወጣቶችን በሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑንም ነው ያስረዱት።
ዘጋቢ፦ ሥራው ድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here