ወጣቶች የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የሚፈቱበት ሥርዓት አባ ሃጋ።

0
86
ባሕር ዳር፡ የካቲት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አለመግባባት እና ግጭት ተፈጥሯዊ ክስተቶች ናቸው፤ በየትኛውም የማኅበረሰብ ክፍል፤ በማንኛውም ቤተሰብ እና በግለሰቦች መካከል ሊፈጠሩ ይችላሉ።
በዚህ የተነሳም በኹሉም ማኅበረሰብ ዘንድ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንደ ባሕል እና ወግ ተቆጥረው ጥቅም ላይ ይውላሉ።
እነዚህ ሥርዓቶች ግጭት እንዳይፈጠር በመከላከል፤ የተበደለውን አስክሰው፥ በዳይን ቀጥተው የተጣላን በማስታረቅ፤ ደም በማድረቅ፤ ፍቺ እንዳይፈጸም እና ቤተሰብ እንዳይበተን በማድረግ የማኅበረሰብን ሰላም ይጠብቃሉ፤ ሀገርንም ያስቀጥላሉ።
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በባቲ ወረዳ ማኅበረሰብ ዘንድ አገልግሎት ላይ የሚውለው “አባ ሃጋ” ባሕላዊ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓት በዚህ ረገድ የሚጠቀስ ነው።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ከአሚኮ የአርሶ አደሮች ወግ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር ቆይታ ባደረጉበት ወቅት ስለ አባ ሃጋ ሲናገሩ አባ ሃጋ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ቦታ የሚሰጠው፤ ወጣቶች የሚያከብሩት፤ ጥሩ ስም እና ዝና እንዲኹም ስክነት እና ብስለት ያለው ወጣት ተመርጦ የተጣሉ ወጣትች የሚዳኙበት ሥርዓት ነው።
የሀገር ሽማግሌዎቹ እንደገለጹት አንድ ወጣት “አባ ሃጋ” ኾኖ የሚመረጠው 18 ዓመት ሲሞላው ጀምሮ እንደኾነ እና እስከ 35 ዓመቱ ድረስ እንደሚያገለግልም ተገልጿል። 35 ዓመት ሲሞላውም መስፈርቱን በሚያሟላ ሌላ ወጣት ይተካል ነው ያሉት።
“አባ ሃጋ” በአካባቢው ወጣቶች መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ቀድሞ የመከላከል፤ ግጭት ሲፈጠር ደግሞ ጣልቃ ገብቶ የማስታረቅ፤ የበደለውን የመቅጣት እና ተበዳይን የማስካስ ሥራ እንደሚያከናውንም ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ለእነዚህ ባሕላዊ የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች ዕውቅና በመስጠት ለፍትሕ ሥርዓት መረጋገጥ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እየሠራ ይገኛል።
የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ይማም ሰኢድ “አባ ሃጋ” በክልሉ በጥናት ተለይተው ዕውቅና ከተሰጣቸው 15 ባሕላዊ ያለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶች መካከል አንዱ መኾኑን ተናግረዋል።
“አባ ሃጋ” መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም ለረጅም ዘመናት አገልግሎት ላይ ይውል እንደነበር ገልጸዋል።
“አባ ሃጋ” ከሌሎች ለየት የሚያደርገው የወጣቶች ሥርዓት ብቻ መኾኑ ነው ያሉት አቶ ይማም ሽማግሌ ኾኖ የሚመረጠው ወጣት ሲኾን የሚዳኘውም የወጣቶችን ጉዳይ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ይማም ገለጻ “አባ ሃጋ” በባቲ ወረዳ በወጣቶች መካከል የሚፈጠሩ ቀለል ያሉ አለመግባባቶችን ወይም ግጭቶችን በራሳቸው የሚፈቱበት ሥርዓት ነው። ግጭቱ ከፍ ያለ ከኾነ በአካባቢው እንደ አበጋር እና ረከቦት ባሉ የሽምግልና ሥርዓቶች እንደሚዳኝም ተናግረዋል።
“አባ ሃጋ” ለረጅም ዘመናት ሲያገለግል ቆይቶ በደርግ ዘመነ መንግሥት ወጣቶች ተሠባሥበው ሲገኙ ለውትድርና ይመለመሉ ስለነበር የወጣቶች መሠባሠብ እየቀየረ እና የ”አባ ሃጋ” ሥርዓትም እየደበዘዘ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ አለመጥፋቱን ያነሱልን አቶ ይማም በባቲ ወረዳ ገጠራማ አካባቢዎች በተወሰኑ ቀበሌዎች ተፈጻሚ እየኾነ እንደሚገኝም አቶ ይማም ገልጸዋል።ሥርዓቱ እንዲሰፋ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
ለ “አባ ሃጋ” ባሕላዊ የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓት ዕውቅና መስጠት ያስፈለገው፦
👉 ወጣቶች የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመፍታት ባሕላቸውን እንዲያዳብሩ ስለሚያስችል።
👉 ወጣቶች ለሀገር ሽማግሌዎች ዕውቅና እየሰጡ ባለመኾናቸው እና ከባሕላዊ የአለመግባባት ሥርዓት ይልቅ ዘመናዊውን የሚመርጡ ወጣቶች እየተፈጠሩ በመኾናቸው “አባ ሃጋ” ለሌሎች አካባቢዎች ትምህርት የሚሰጥ በመኾኑ።
👉 ወጣቶች ባሕላቸውን የሚያከብሩበት፤ በባሕላቸው የሚዳኙበት ዕድል ስለሚፈጥር መኾኑንም ነው የጠቀሱት።
አቶ ይማም የ”አባ ሃጋ” ባሕላዊ የአለመግባባት ሥርዓት ከሌሎች ሥርዓቶች ለየት ያለ በመኾኑ በሥልጠና፣ በቁሳቁስ እገዛ እና ክትትል በማድረግ እንዲጠናከር እና በበቂ ሁኔታ ዕውቅና እንዲያገኝ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
የባሕላዊ ፍርድ ቤቶች አማካሪ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ “አባ ሃጋ” በማኅበረሰቡ ዘንድ በውል እንዲታወቅ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው በአግባቡ ይከናወናል ብለዋል።
አማካሪ ምክር ቤቱ ባሕላዊ የአለመግባባት መፍቻ ሥርዓቶችን የማስተካከል ሥልጣን አልተሰጠውም ያሉት አቶ ይማም ነገር ግን ማኅበረሰቡ ሲገለገልባቸው በነበረው ልክ አስጠብቆ የማስቀጠል እና የጎደላቸውን ነገር እየሞሉ የማኅበረሰቡን ችግሮች እንዲቀርፉ የማስቻል ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
አሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here