“ድርጎኛ” የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን የመጠበቂያ ባሕላዊ ሥርዓት።

0
59
ባሕር ዳር፡ የካቲት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ባሉት ብርቅዬ እንሰሳት፣ ባለው ድንቅ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ በውስጡ ባለው ብዝኀ ሕይወት የዓለምን ቀልብ የሳበ ፓርክ ነው።
በ1971 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት(ዩኔስኮ) መመዝገብም ችሏል። በዩኔስኮ የተመዘገበው የፓርኩ ስፋትም 136 ስኩየር ኪሎ ሜትር እንደነበር የፓርኩ መረጃ ያሳያል።
ነገር ግን ብርቅዬ እንሰሳትም ኾኑ ማራኪ መልክዓ ምድሩ በዩኒስኮ ከተመዘገበው ክልል ውጭም ይገኙ ስለነበር ፓርኩ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ማስፋፊያ ሲደረግለት ቆይቷል። አሁን ላይ ወደ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር እንዲሰፋም ተደርጓል። የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በፓርኩ ተጨማሪ ማስፋፊያ በማድረግ በዩኔስኮ ዳግም ለማስመዝገብ እየሠራ መኾኑንም አስታውቋል።
የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የሕግ ማስከበር ባለሙያ ሲሳይ ሰለሞን በማስፋፊያው በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ፓርኩ ማሟላት ያለበትን ጉዳይ በመለየት የተለያዩ ሥራዎች ሢሠሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በተለይ ፓርኩ ያለውን አካባቢያዊ እና ሀገራዊ ፋይዳ ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር በኩል ውጤታማ ሥራ ተሠርቷል ነው ያሉት።
ማኅበረሰቡ ፓርኩን የሚጠብቅበት “ድርጎኛ” የተሰኘ ሥርዓት እንዳለው ጠቁመዋል። ይህም በፓርኩ አዋሳኝ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች ማኅበረሰቡ የተፈጥሮ ሃብቱን የሚጠብቁ ሰዎችን በመምረጥ እና ለተመረጡት ሰዎች እህል እና ገንዘብ በማዋጣት የተፈጥሮ ሃብትን የሚጠብቁበት የቆዬ ሥርዓት እንደኾነ ገልጸዋል።
የሃይማኖት አባቶችን በመጠቀም ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን የማውገዝ ሥራ መከናወኑንም ገልጸዋል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገዬ (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው እንደ ትምህርት ተቋም ባለሥልጣኑ ፓርኩን ዳግም በዩኒስኮ ለማስመዝገብ ሲያከናውን የነበረውን ሰፊ የማስፋፊያ ሥራ ሲያግዝ መቆየቱን ተናግረዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከተቋማት ጋር በመቀናጀት በፓርኩ ጥናት እና ምርምር በማድረግ፣ የፓርኩን ቦታ በማስፋት እና የዱር እንሳሳት ጥበቃውን ሊያጠናክሩ የሚችሉ ሥራዎችን በትብብር መሥራቱን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የቱሪዝም እና ቅርስ አሥተዳደር ትምህርት ክፍል ከፍቶ እየሠራ መኾኑን ያሳወቁት ፕሬዝዳንቱ ተማሪዎች ተግባራዊ ትምህርት የሚያገኙበት፣ መምህራን ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉበት ቦታ ነው ብለዋል።
በፓርኩ ላይ የመማር ማስተማር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እንደሚያከናውኑም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የዱር እንሰሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ በበኩላቸው በዩኔስኮ የሚመዘገብ ቦታ ልዩ መኾኑ ተረጋግጦ በሌሎች ዓለማት የሌሉ መልክዓ ምድሮች፣ የዱር እንሰሳት፣ እጽዋት እና መሰል ጉዳዮች ሲኖሩት ነው ብለዋል።
አቶ ኩመራ በፓርኩ የተደረገውን ማስፋፊያ ጨምሮ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ አስፈላጊ የኾኑ መስፈርቶች መመረጣቸውን ገልጸዋል።
በውስጡ ያለ ሥነ ውበት ለየት ያለ ሥፍራ መኾኑ፤ በፓርኩ ውስጥ ብቻ የሚገኙ የእንሰሳት እና እጽዋት ዝርያዎች ብሎም ሌሎች ጉዳዮች ሳይንሳዊ ትንተና ተደርጎባቸዋል ብለዋል። መስፈርቶቹ የፓርኩን ማስፋፊያ ተቋሙ እንዲቀበለው የሚያስችሉ እንደኾኑም ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ ከነበረው ላይ ማስፋፊያው ተጨምሮ በዩኔስኮ ሲመዘገብ ለፓርኩ አዲስ አቅም ይፈጥራል። የዓለም ቅርስ መኾኑን ያጠናክራል። ዓለም ስለ ፓርኩ እንዲያስብ እና እንዲጨነቅ ዕድል እንደሚፈጥርም አብራርተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here