ባሕር ዳር፡ የካቲት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዋልያ በኢትዮጵያ በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚገኝ ብርቅ እንስሳ ነው። የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኒስኮ) እንዲመዘገብ ካደረጉት መካከል በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኘው ዋልያ ግንባር ቀደሙን ቦታ ይይዛል።
ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በፓርኩ የሚገኙት የዋልያ ብዛት ከ650 በላይ እንደነበር ከብሔራዊ ፓርኩ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ኾኖም በሰሜኑ ጦርነት እና በአማራ ክልል በተፈጠረው ግጭት ሳቢያ በሚፈጸሙ ሕገ ወጥ አደኖች እና በሌሎች ችግሮች ምክንያት በከፍተኛ ኹኔታ እንደቀነሰ ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።
ግጭቱ በፓርኩ የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲቀንስ በማድረግ እና በፓርኩ ውስጥ የሚደረጉ ጥበቃዎችን አስተጓጉሎ ስለነበር ዋሊያዎቹ ችግር እንዲያጋጥማቸው አድርጓል።ችግሩን በመቅረፍ የዋሊያ ቁጥርን ለመጨመር እና ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ ፓርኩ ከመንግሥት፤ ከአጋር አካላት እና ከማኅበረሰቡ ጋር እየሠራ ይገኛል።
የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የሕግ ማስከበር ባለሙያ ሲሳይ ሰለሞን የዋሊያን ቁጥር በተለያዩ ምክንያቶች መቀነሱን አንስተዋል። የብርቅየ ዋሊያ ቁጥር መልሶ እንዲያገግም እንደ ሀገር ዕቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል።
7ሺህ አባላት ያሉት የኢኮ ቱሪዝም ማኅበር፣ የሚሊሻ ኀይሎች፣ የጓሳ አደረጃጀቶች እና ሌሎች ማኅበራት ፓርኩን በመጠበቅ ላይ መኾናቸውን አንስተዋል። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲም ከፓርኩ ጋር በቅርበት እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
የሰሜኑ ጦርነት እና በክልሉ ያለው ግጭት ለዋሊያ ቁጥር መቀነስ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ጠቁመዋል። በቅርቡ በተጠና ጥናት ከ275 እስከ 300 የሚደርሱ ብርቅየ ዋሊያዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
ዋሊያ በሚኖርበት አካባቢ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ከፓርኩ እና ከብርቅየው ዋሊያ የሚያገኙትን ጥቅም በማሳወቅ እንዲጠብቁት የማንቃት ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል። በፓርኩ የጸጥታ አካላት ቅንጂታዊ የጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኩመራ ዋቅጅራ የዋሊያ ሕልውናን ለማስጠበቅ ጥበቃዎችን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ መኾኑንም ተናግረዋል።
ብሔራዊ የብርቅየ ዋሊያ ስትራቴጅ ዕቅድ በማውጣት፣ ችግሮችን በመለየት፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እና ችግሩን መቅረፍ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልጸዋል።
በብርቅየ የዋሊያ እንስሳ ላይ ሕገወጥ ተግባር የሚፈጽሙ አካላትን ለሕግ የማቅረብ ሥራ በማከናወን ኀብረተሰቡ የዋሊያ አምባሳደርነቱን እያሳየ መኾኑን ጠቁመዋል። ብርቅየ የዋሊያ እንስሳትን ከመጥፋት ለመታደግ እየተሠራ ነውም ብለዋል።
መንግሥት የዋሊያ ደኅንነትን ለማስጠበቅ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









