በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሰንበቴ ማኅበር መጀመሪያ።

0
74

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ ወረዳ የሚገኘው ጥንታዊው ኤልሻማ ደብረማህቶት መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በውስጡ በያዛቸው ብርቅዬ ንጉሳዊ ቅርሶች፣ አስደናቂ የሕንፃ ጥበብ እና ታሪካዊ ዳራው የቱሪዝም መዳረሻ እየኾነ መጥቷል።

የቤተክርሲቲያኑ የስብከተ ወንጌል መምህር እና የቅርስ አስተዋዋቂ መጋቢ ጥበባት ዳኘ ብርቄ ለአሚኮ ዲጁታል እንደገለጹት ቤተክርስቲያኑ የተመሠረተው በ562 ዓ.ም በአጼ ወሰን ሰገድ ማህረነ ክርስቶስ ዘመነ መንግሥት ነው።

ስፍራው ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር በሚወስደው መንገድ ላይ በመኾኑ ለዘመናት የታላላቅ ነገሥታት መዳረሻ እና ማረፊያ ኾኖ ቆይቷል።

እንደ መጋቢ ጥበባት ገለጻ ታላቁ ንጉሥ አጼ ዘርአ ያዕቆብ በአካባቢው ሲያልፉ በተፈጥሮ ውበቱ ተስበው በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሰንበቴ ማኅበር በዚህ ስፍራ እንደመሠረቱ ይነገራል። ቤተክርስቲያኑ በ1522 ዓ.ም የመቃጠል አደጋም ገጥሞት ነበር።

በኋላም የእቴጌ ጣይቱ ወንድም ራስ ወሌ በጽድ እና በቆዳ አሳምረው አሳንጸውታል።

ቤተክርስቲያኑ ከዓድዋ ድል ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ሲኾን ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ወደ ጦርነቱ ከመዝመታቸው በፊት በቤተክርስቲያኑ ሰባት ቀን ሱባኤ መግባታቸው ይነገራል።

ከድል በኋላም ለቤተክርስቲያኑ 150 ጋሻ መሬት በመስጠት እና አገልግሎቱን በማጠናከር ውለታቸውን ከፍለዋል።

አሁን የሚታየው ሕንጻ በ1922 ዓ.ም በንግሥት ዘውዲቱ ተጀምሮ፣ እርሳቸው ካለፉ በኋላ በአጼ ኃይለ ሥላሴ የተጠናቀቀ ሲኾን፤ ግንባታው የተከናወነበት የድንጋይ፣ የኖራ እና የቆዳ ማጣበቂያ ጥበብ ለዘርፉ ምሁራን አስደናቂ ኾኖ ቆይቷል።

በአሁኑ ወቅት በቤተክርስቲያኑ ሙዚየም ውስጥ በርካታ ቅርሶች ተጠብቀው ይገኛሉ። ከእነዚህም መካከል፦

👉የአጼ ምኒልክ እጀ ጠባብ፣ የሱፍ ካባ እና የብር መስቀሎች

👉የንግሥት ዘውዲቱ አልባሳት

👉የአጼ ኃይለ ሥላሴ የጸሎት ምንጣፍ (ስጋጃ)፣ ጦርና ጋሻ

👉ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እና ልዩ ልዩ የብር ዕቃዎች ይገኙበታል።

በጃማ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ይልማ ታደለ እንደገለጹት ቤተክርስቲያኑ በሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እና ባሕላዊ ቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም አለው።

ቅርሱ በአግባቡ ተጠብቆ ቢተዋወቅ ለአካባቢው ማኅበረሰብ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ የክልሉን የቱሪዝም ገቢ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።

ይሁን እንጂ ሀገራዊ ግጭቶች እና አለመረጋጋቶች ቅርሱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ እና የጥበቃ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ትልቅ ተግዳሮት እንደኾኑባቸውም ቡድን መሪው ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ሰናይት በየነ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here