ተፈጥሮ ያስጌጠው አባ አስራት ገዳም።

0
101

 

ባሕር ዳር፡ የካቲት 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎‎በኢትዮጵያ ከሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎች መካከል አባ አስራት ገዳም አንዱ ነው። ጥንታዊው አባ አስራት ገዳም በአማራ ክልል በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በተድላ ጓሉ ክፍለ ከተማ ይገኛል። ይህ ገዳም ከጥንታዊቷ ደብረ ማርቆስ ከተማ በግምት አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ አባ አስራት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው የሚገኘው።

የአባ አስራት ገዳም መምህር ወልደ ማርያም ከበደ ገዳሙ በ1515 ዓ.ም መመሥረቱን ለአሚኮ ዲጂታል ገልጸዋል። ይሁን እንጅ ቤተክርስቲያኑ በገጠመው የቃጠሎ አደጋ ጠፍቶ እና ሥፍራው ተረስቶ ለ200 ዓመት ያህል ቆይቷል ይላሉ።

ከዓመታት በኋላ አባ አስራት የተባሉ ሰው በልጅነታቸው ወደ ዋልድባ ገዳም አቅንተው የቤተ ክህነት ትምህርት እየተማሩ እያለ በወቅቱ የነበሩት የቤተ ክህነት መምህር ያንተ ቦታ እዚህ አይደለም ወይን ባለበት ቦታ ከጨሞጋ አፋፍ ነው ተባሉ ይላሉ።

ከዚያም አባ አስራት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ አክብረው ጉዞአቸውን ጀመሩ እና የተባሉት የወይን ቦታ ደረሱ። ብዙ ጸሎት አደረጉ፤ በዚያም የወንበር ቅርጽ ባላት ድንጋይ ተቀመጡ ይላሉ። ከዚያም ቦታው ላይ በ1815 ዓ.ም መነኩሴው አባ አስራት ስፍራውን እንደገና መመሥረታቸውን ያስረዳሉ።

የመድኃኔዓለምን ቤተክርስቲያንም አነጹ። ጥቅምት 27 እና መጋቢት 27 በዓመት ሁለት ጊዜ በዓሉ በድምቀት ይከበራል። በዚህ ታላቅ ገዳም ስር የሚፈልቀው
ጸበልም ለብዙዎች ፈዋሽ እንደኾነ ይናገራሉ።
ገዳሙን ሴት እና ወንድ መነኮሳት የበረከት እና የጸሎት ቤታቸው አድርገው ይኖሩበታል ይላሉ።

የጨሞጋ ወንዝን ተንተርሶ የሚገኘው ገዳሙ ለዕይታ ማራኪ፣ መንፈስን የሚያድስ ትልቅ የበረከት ቦታ ነው። የጨሞጋ ወንዝ፣ በዙሪያው የሚገኙ ዛፎች፤ በገዳሙ ያለው በረከት በአንድ ላይ ተስማምተው ተዋደው እና ተጋምደው ለዘመናት ዘልቀዋል።

ይህ ጥንታዊ ገዳም የበረከት መገኛ፤ የመንፈስ ማደሻ ነው። በተለይ በዙሪያው የከበቡት ዛፎች ሲመለከቷቸው ለገዳሙ አረንጓዴ አጥር ከመኾናቸው በተጨማሪ ዕይታን የሚስቡ እና መንፈስን የሚያድሱ ናቸው።

ተፈጥሮአዊ አቀማመጡ አግራሞትን የሚያጭር ድንቅ ምድር፣ ታሪክ የተሠነደበት፣ ታሪካዊ፣ ጥንታዊ እና የተለዬ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ያለው የበረከት ቦታ ነው ይላሉ።

የጎጃም ንጉሥ የነበሩት ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከገዳሙ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንደነበራቸው እና ገዳሙን ለማጠናከር ውለታ እንደነበረባቸው ነግረውናል። በገዳሙ የሚገኙ ዕቃዎች የሚቀመጡበት የእቃ ቤትም በንጉሡ እንደተሠራ ገልጸዋል።

የገዳሙ ቤተክርስቲያን በወቅቱ በነበረው የኪነ ሕንጻ ጥበብ፣ በጥንታዊ የበረሃ ዛፍ እና በጥርብ ድንጋይ እንደተሠራ ነው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅት በገዳሙ የእቃ ቤት ውስጥ በርካታ ቅርሶች ይገኛሉ። ከእነዚህም ውስጥ

👉 የወንበር ቅርጽ ያላት ድንጋይ ማለትም አባ አስራት የተቀመጡባት እና ጸሎት ሲያደርጉባት የነበረች።

👉ልዩ ልዩ ጥንታዊ መስቀሎች

👉 የተለያዩ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እና ሌሎች ጥንታዊ ቅርሶች የሚገኙበት ነው።

በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያ በላቸው አስማረ በከተማ አሥተዳደሩ ስር የሚገኙ
ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ስፍራዎችን በማስተዋወቅ እና በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ወቅታዊ ችግሩ ፈታኝ ቢኾንም ገዳሙን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው፤ ይህም ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሚናው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here