ቦታው በተፈጥሮው ግርምትን ያጭራል፤ ውስጡም ታሪክን ሰንዶ የያዘ የታሪክ ማኅደር ነው። ተፈጥሮ ይደነቃል፤ የፈጣሪም ተዓምር በተግባር ይታያል በቅድስት ወለተ ጴጥሮስ አንድነት ገዳም።
የቅድስት ወለተ ጴጥሮስ አንድነት ገዳም በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዳንግላ ወረዳ ይገኛል። ከዳንግላ ከተማም በ17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወንደፋይ በተባለ ቀበሌ ነው የሚገኛው።
መነኮሳት ለዘመናት በጽናት የዘለቁበት ጥንታዊ እና ታሪካዊ ሥፍራ ነው። የዳንግላ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ቦጋለች ፋንታሁን እንደሚገልጹት የጻድቋ ወለተ ጴጥሮስ አንድነት ገዳም በሰንሰለታማ ተራራሮች ተከቦ በሸለቆማ ስፍራ የተመሠረተ ድንቅ ሥፍራ ነው።
በርካታ ልዩ ገጽታዎች አሉት ነው የሚሉት። ገዳሙ በአጼ ሱስንዮስ ዘመነ መንግሥት በ1607 ዓ.ም በጻድቋ ወለተ ጴጥሮስ እንደተመሠረተ ይነገራል።
ቅድስት ወለተ ጴጥሮስ ከአፋፍ ላይ ወደ ዋሻ የተወወረችበት ትልቅ አለታማ ድንጋይ ለታሪክ ቅርስነት፣ ለአማኞች ፈውስ እና የመንፈስ ማደሻ ኾኖ እያገለገለ ይገኛል። በተለይም ጻድቋ የተወረወረችበትን ምክንያት በማድረግ ገዳሙ እንደተመሠረተ ይነገራል ነው ያሉት።
ገዳሙ ውስጥ ለመድረስም ወደ ዋሻው ወደታች መቶ ሜትር በእግር መጓዝ እንደሚያስፈልግም ያስረዳሉ። ገዳሙ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እና ንዋየ ቅዱሳት ማኅደር ነው። በዙሪያው ሀገር በቀል ዕፅዋት፣ የተለያዩ የዱር እንስሳት እና አዕዋፍ በጋራ ተጋምደው ይገኙበታል። በገዳሙ የገዳማውያንን ጥንካሬ እና ሥራ ወዳድነት የሚያሳይ የግብርና እና የእንሰሳት እርባታም በስፋት አለ።
ተስማሚ የአየር ሁኔታ ያለው ውብ ሥፍራም ነው። ከተራራው አፋፍ ወደ ታች ሲታይ ለመውረድ የማይቻል የሚመስል ነገር ግን ሲጓዙ ድንቅ ተፈጥሮን የሚያስቃኝ ማራኪ አቀማመጥ ያለው ነው። ይህ ድንቅ የተፈጥሮ እና የታሪክ ማኅደር አዕምሮ የሚያድስ፣ መንፈስ የሚያረካ፣ በረከትን የሚያስገኝ እና አዲስ ገጽታን መገንባት የሚያስችል ነው።
ቦታውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ፣ ለማስተዋወቅ እና በዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
የገዳሙ ዓመታዊ ክብረ በዓል በየዓመቱ ኅዳር 17 ቀን ከተለያዩ አካባቢዎች በሚመጡ የሃይማኖቱ ተከታዮች በድምቀት ይከበራል።
ቦታው ጥንታዊ እና ታሪካዊ ከመኾኑም በተጨማሪ ለተለያዩ ለጥናት እና ምርምር ሥራዎች የሚያገለግል መኾኑም ተገልጿል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









