የሃይማኖት እና የጽናት ዓምድ፣ የዘመናት ታሪክ ማኅደር የኾነው የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መሠረቱ የተጣለው በአጼ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በእነማይ ወረዳ ከብቸና ከተማ ጥግ የሚገኘው ይኸው ሥፍራ በአባ በኪሞስ (ተከስተ ብርሃን) ነው የተመሠረተው። በአጼ ይስሐቅ ዘመን የተጠናከረው ገዳሙ የሊቃውንት መኖሪያ እና የመንፈሳዊ ዕውቀት ማዕከል ኾኖ ዘልቋል።
በመላ ኢትዮጵያውያን በፍቅር እስከ መቃብር የታወቀውን የዲማ ጊዮርጊስ ገዳም ከምናብ ባሻገር በአካል ለማሳየት እና ለዕንቁ ቅርሶቹ ማረፊያ ሙዚየም እየተገነባ ነው።
የእነማይ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቅርጽ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ ደስታ ገብረመድህን እንደገለጹት ይኸው የሙዚየም ግንባታ 95 በመቶ ላይ ደርሷል። ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የኾነበት ሙዚየሙ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚኾነው ከኅብረተሰቡ የተገኘ ነው። ይህም ትውልዱ በታሪክ ብቻ የሚኖር ሳይኾን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ መነሳቱን የሚያሳይ ነው።
ሙዚየሙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ፣ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ከቅርስ ጥበቃ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ነው።
የሕንፃው ዙሪያ እና የኤሌክትሪክ ሥራዎች የተጠናቀቁ ቢኾንም የውስጥ መደርደሪያዎች፣ ዲጂታል ካሜራዎች እና ለጥንታዊ የግድግዳ ስዕሎች ጥገና አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ የፍቅር እስከ መቃብርን ዘላለማዊ ትርክት ከታሪካዊ አሻራዎች እና ውድ ቅርሶች ጋር ለማስተሳሰር የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን መጎብኘት የመጽሐፉ አንባቢያን ታሪካዊ ኀላፊነት ነው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









