አወይቱ የተፈጥሮ ፍል ውኃ

0
53

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 02/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አወይቱ ፍል ውኃ በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ይገኛል። ከሰንበቴ ከተማ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ 4 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚገኝ ድንቅ የተፈጥሮ መስህብ ነው፡፡

ፍል ውኃው ናዛሮ እና ቀቢ በተባሉ ወንዞች መካከል ላይ ይገኛል። ከአለታማ ስፍራ ከሚፈልቀው ፍል ውኃ የሚወጣው እንፋሎት ከነጎድጓዳማ ድምጹ ጋር ተዳምሮ ለአካባቢው ልዩ ውበትን ፈጥሮለታል፡፡

ዙሪያው ደጋጋ፣ ኮሎ፣ አያበር እና አጎብዲ በተባሉ ተራራዎች የተከበበ ቦታ ነው። ፍል ውኃው ከተራራዎች ላይ ሲመለከቱት ጥጥ መስሎ ይታያል፡፡ ከሩቅ ሲያዩት የደመና ጉም ይመስላል። ከቦታው ላይ ደረሰው ሲመለከቱት ግን ከምድር የሚፈልቅ ውኃ እና እንፋሎት ያለበት እና ሲነኩት ደግሞ ሙቅ የኾነ ነው።

ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያለው በመኾኑ በ15 ደቂቃ ውስጥ ሥጋ፣ በቆሎ እና እንቁላል የመሳሰሉ የምግብ አይነቶችን እነደሚያበስልም ይነገራል፡፡ ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ችሮታ የቱሪስቶችን ቀልብ ይስባል።

በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጀማል ሐሰን አወይቱ ፍል ውኃ በ1953 ዓ.ም አካባቢ እንደፈለቀ ይነገራል ብለዋል።

ከአካባቢው መልከዓ ምድር ጋር ተዳምሮ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ አንዱ የቱሪስት መስህብ ስለመኾኑም ነው የጠቆሙት። ከፍል ውኃው በሚወጣው ጭስ የአካባቢው ሰዎች የደከመ ሰውነታቸውን ለማፍታታት፣ ውበታቸውን ለመጠበቅ እና ከተለያዩ በሽታዎች ለመፈወስ እንደሚጠቀሙበትም ገልጸዋል።

ከአካባቢው ማኅበረሰብ በተጨማሪ ከአፋር፣ ከሰሜን ሸዋ እና ከሌሎችም አካባቢዎች የሚመጡ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መዳረሻ ስለመኾኑም ነው የተናገሩት።

ፍል ውኃውን ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር ለማልማት እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በዕቅድ ተይዞ እየተሠራ ስለመኾኑም አመላክተዋል።

ዘጋቢ፦ አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here