ተፈጥሮ ያሳመረው ዶንዶር ፏፏቴ

0
48
ባሕር ዳር: መጋቢት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ የመስህብ ሃብቶች ያሉት አካባቢ ነው፡፡
በአካባቢው ከሚገኙ የመስህብ ሃብቶች መካከል ፏፏቴዎች፣ ሐይቆች፣ ጥብቅ ደኖች፣ ተራራዎች፣ ጥንታዊ ገዳማት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከሚገኙ በርካታ ፏፏቴዎች ውስጥ ደግሞ የዶንዶር ፏፏቴ ተጠቃሽ ነው፡፡ ፏፏቴው ከቻግኒ ከታማ አሥተዳደር በምሥራቅ አቅጣጫ ከቻግኒ- ዚገም በሚወስደው መንገድ በተለምዶ “መጠለያ ሰፈር” ከሚባለው አካባቢ በግምት 1 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ከከተማዋ ወደ ፏፏቴው ለመሄድ የመንገድ መሠረተ ልማት የተሟላለት ነው፡፡
ፏፏቴው ከላይ ወደ ታች እስከ 35 ሜትር ሲወረወር ለሚመለከት ሁሉ ልዩ ስሜት ይፈጥራል፡፡ የዶንዶር ፏፏቴ መነሻው የዶንዶር ወንዝ በመኾኑ ስያሜውን ከወንዙ እንዳገኘም ይነገራል።
ከአካባቢው ነዋሪ አቶ ዘውዴ ተሾመ ዶንዶር ፏፏቴ ከላይ ተወርውሮ ወደ ታች ሲወርድ ልዩ ስሜት የሚፈጥር ነው ይላሉ፡፡ በተለይ በክረምት ወራት ዙሪያ ገባው በአበባ አሸብርቆ ፏፏቴው በሚፈጥረው ቀስተ ደመና መዝናናት ልዩ ስሜት እንሚሰጥ ተናግረዋል።
ዶንዶር ፏፏቴ አቅም ላላቸው ባለሃብቶች ተሰጥቶ በአካባቢው ሎጅ እና መዝናኛ ቢገነባ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ትልቅ ሃብት እንደኾነ ነው የተናገሩት።
ሌላው የቻግኒ ከተማ ነዋሪ ዳንኤል ያዘው ዶንዶር ፏፏቴ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ፤ የሃብት ምንጭም የሚኾን እና መታየት ያለበት ሃብት መኾኑን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ውበቴ ካሳሁንም ዶንዶር ፏፏቴ በወርሐ መስከረም መስቀል አካባቢ በርከት ያሉ የጎበኝዎች ቁጥር የሚስተናዱበት ቦታ ነው ብለዋል።
የአካባቢው ሁኔታ ጎብኝን በሚመጥን መንገድ እንዲጠበቅ መሥራት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም ልማት ባለሙያው ተሰማ ታዝበው በወቅታዊው የሰላም እጦት ምክንያት የዶንዶር ፏፏቴ የጎብኝዎች ቁጥር መቀነሱን ተናግረዋል።
ጽሕፈት ቤቱ ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ ዙሪያውን አጥር ማሳጠር፣ መንገድ ማስተካከል እና መብራት እንዲገባ ማድረግ መቻሉንም አንስተዋል።
ዘጋቢ፡-ሰለሞን ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here