የታሪካዊ ቅርሶች መገኛ ጥንታዊው ቤተክርስቲያን

0
11

 

ባሕር ዳር: መጋቢት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ደብረ ገነት ቅዱስ ኤሊያስ ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ማርቆስ ከተማ በ45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ በደብረ ኤሊያስ ወረዳ የሚገኝ ጥንታዊ እና ታሪካዊ ደብር ነው።

ደብሩ በ1466 ዓ.ም በአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመን እንደተመሠረተ ታሪክ ይናገራል። የቅኔ እና የዜማ ትምህርት ማዕከል ኾኖ አገልግሏል። እንደ አቡነ ቴዎፎሎስ፣ ሀዲስ አለማየሁ ፣ መላኩ በጎሰው፣ ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሴ እና ሌሎችንም ልሂቃን ያፈራ ታሪካዊ ቦታ ነው።

የደብረ ገነት ቅዱስ ኤሊያስ ደብር አሥተዳዳሪ ድማህ ገነት አዳነ ጥላሁን በአጼ ዘርዓያዕቆብ ዘመን ድል አሰማ የተባሉ ሰው ከሼዋ ሲመጡ ታቦተ ኤሊያስን እና ከብቶችን ይዘው ወደ ጎጃም አቀኑ ይላሉ።

ማቻከል ከደረሱ በኋላ ታቦቱን የሚያስቀምጡበት ቦታ አሰቡ። ጉዟቸውንም ቀጠሉ። አሁን የቅዱስ ኤሊያስ ቤተክርስቲያን ከተሠራበት ቦታም ደረሱ። በዚያም አርፈው አደሩ። ሲነጋም ወደ ሌላ ቦታ ሊያቀኑ ሲነሱ ከከብቶች መካካል ኮርማው ወይም የከብቶቹ አውራ በሬ ከተኛበት አልነሳም አለ ይላሉ። በዚያ መነሻነትም የታቦተ ኤሊያስ ማረፊያ ቦታ ይህ ነው በማለት አሁን ካለበት ላይ እንደ ተመሠረተ ይነገራል ብለዋል።

ቅዱስ ኤሊያስ ደብር የተገነባው በጥንታዊ ኪነ ሕንጻ ጥበብ ባላቸው ሰዎች በጭቃ ጡብ እና በጥንታዊ እንጨት የተሠራ ነው ይላሉ። ውጫዊው ደግሞ በዘመኑ ኪነ ሕንጻ በድንጋይ እና በሌሎችም ተሠርቷል ነው ያሉት።

በዚህ ቦታ ትልቅ በረከት የሚገኝበት መኾኑን የተናገረት የደብሩ አሥተዳዳሪ በየዓመቱ ታኅሣሥ 01 ዓመታዊ ንግሡ በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር ነው የተናገሩት።

በደብሩ የተለያዩ ጥንታዊ ቅርሶች ይገኙበታል። ከነዚያም መካከል፦

👉 የአቡነ ቴዎፍሎስ የጸሎት ቤት አሁን የእቃቤት ኾኖ የሚያገለግል፤

👉 ሙሽራው እና ሙሽሪት ድንጋይ፤

👉 ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እና በከበሩ ማዕድናት የተሠሩ መስቀሎች፤

👉 ሕሙማንን የሚፈውስ ፀበል እና ሌሎች ሃብቶችን አቅፎ ዩያዘ ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ነው።

በዚህ ስፍራ የቅኔ እና የአቋቋም የቤተ ክህነት ትምህርት እንደሚሰጥም አሥተዳዳሪው ተናግረዋል። ደብሩ ሲመሠረት ከነበሩት ዘጠኝ የፅድ ዛፎች አሁን ላይ ሁለት ፅዶች እና ጥንታዊ የዝግባ ዛፎች በዙሪያውም እንዳሉ ገልጸዋል።

የአፄ ዮሐንስ እንዚራ እና ከደብሩ ውስጥ የወቅቱን ጥበብ ገልጠው የሚያሳዩ፤ ወደ ኋላ የሚመልሱ የግድግዳ ላይ ስዕሎች እና ሌሎችም ይገኙበታል።

የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ አለሽ ሽታ ደብሩ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለው መኾኑን ተናግረዋል። የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ አንደኾነም ተናግረዋል።

በደብሩ የሚገኙ ቅርሶችን ለመጠበቅ የምዝገባ ሥራዎች መሠራታቸውንም አንስተዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here