ጅቦች ከሰው ለምደው በሰላም የሚኖሩባት ድንቅ ከተማ

0
80
ባሕር ዳር: ግንቦት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለማችን ላይ የዱር እንስሳት እና የሰው ልጅ በአንድ መንደር እና በቅርብ ርቀት አብረው ይኖራሉ ቢባል ለማመን የሚከብድ ሊኾን ይችላል። ነገር ግን ይህንን አስገራሚ እውነታ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በተግባር አሳይታናለች።
ሐረር ስትታወስ አብሮ የሚነሳው የጀጎል ግንብ ብቻ አይደለም፤ ከጀጎል ግንብ በስተጀርባ የሚኖረው የጅብ ትርኢት እና ከሰዎች ጋር ያላቸው የዘመናት ሰላማዊ ትስስርም ጭምር እንጂ።
👉የከተማዋ “ሌሊት ጠራጊዎች” ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሐረሪ ክልል ባሕል፣ ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ ተወለዳ አብዶሽ ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሐረር ጀጎል ግንብ ውስጥ ጅቦች ከማኅበረሰቡ ጋር ተላምደው እንደሚኖሩ ተናግረዋል።
በሌሎች አካባቢዎች ጅብ አስፈሪ እና አደገኛ አዳኝ ተደርጎ ቢፈራም በሐረር ግን የሰላም እና የጥበቃ ምልክት ነው ይላሉ ኀላፊው።
ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ በጥንታዊው የጀጎል ግንብ ላይ ለጅቦች ብቻ ተብሎ የተሠራ ራሱን የቻለ ልዩ መግቢያ እና መውጫ በር (ቀዳዳ) መኖሩ ነው።
በየቀኑ ፀሐይ ስትጠልቅ እና ሌሊቱ ሲተካ እነዚህ የዱር እንስሳት በዚህ ጥንታዊ በር በኩል በነጻነት ወደ ከተማዋ ይገባሉ፤ ሲፈልጉም ይወጣሉ ብለውናል።
ለዘመናት በኖረው በዚህ ልምድ ውስጥ ጅቦቹ በውውም ኾነ በቤት እንስሳት ላይ ምንም ዓይነት ትንኮሳ እና ጥቃት አድርሰው አያውቁም ነው ያሉት ኀላፊው።
ይልቁንም ሌሊት ከተማዋን በማጽዳት እና ከተለያዩ ተባዮች በመጠበቅ ረገድ የማይተካ ምስጥራዊ ውለታ ለከተማዋ ያበረክታሉ ነው ያሉት።
👉 የጅብ መጋቢዎቹ አስደናቂ ምስጢር፦
ሐረሬዎች በጨለማ ጅቦችን እየጠሩ ስጋ በእጃቸው እያጎረሱ ለጅቦቹ የሚመግቡበት ጥበብ የሰውን ልጅ እና የዱር እንስሳትን ግንኙነት አዲስ ትርጉም ያሰጠ ነው።
👉አዲሱ የጅብ መንጋ ማዕከል፦
አሁን ላይ የሐረር ከተማ እና የጅቦችን ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር ይበልጥ ለማጉላት እና የከተማዋን የቱሪስት መዳረሻነት ለማስፋት አዲስ ተስፋ ሰጭ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
በሐረር ጀጎል ግንብ አቅራቢያ አዲስ የጅብ መንጋ ማዕከል በክልሉ መንግሥት መገንባቱን አቶ ተወለዳ አጫውተውናል።
👉 የማዕከሉ ዋና ዓላማ፦
የሰዎችን እና የጅቦችን ዘመናት ያስቆጠረ ወዳጅነት ለሚመጡ ጎብኝዎች በተደራጀ እና ውብ በኾነ መንገድ ማሳየት እንዲሁም ሐረር ያላትን የሰላም፣ የባሕል እና የብዝኀ ሕይወት ተስማምቶ የመኖር ተምሳሌትነት ለዓለም ማስተዋወቅ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here