ባሕር ዳር: ሰኔ 24/2018 ዓ.ም ግርማ ሞገሱ ያስፈራል፤ በዙሪያው እንደ ጋሻ ጃግሬ የሚጠብቁት ተራራዎች🏔 ልዩ ውበትን አጎናጽፈውታል፤ የአዕዋፋቱ ኅብረ ዜማ ልቦናን ይመስጣል።
ሊማሊሞ ጥበብ የተሞላበት ስፌት መሠል መንገድ ነው፡፡ ድብ ባሕር አካባቢ ኾኖ ወደላይ የሊማሊሞን መንገድ ላየው ሰው ተራራው 🏔 ከሰማይ ጋር ኅብረት ፈጥሮ ሰማያዊ የምንጭ ውኃን የሚያወርድ ኃይል ያለው ይመስላል፡፡
ክረምት ከበጋ የማይነጥፉ 🏞ምንጮች እና ጅረቶች የሞሉበት የሊማሊሞ መንገድ ወደ ዛሪማ፣ አዲ አርቃይ ከዚያም ተከዜን ተሻግሮ ወደ ትግራይ የሚያደርስ ኪናዊ የምህንድስና ጥበብ የሚታይበት ጠመዝማዛ መንገድ ነው። የሰሜኑን ክፍል ከመሀል ሀገር የሚያገናኝ መንገድም ነው ሊማሊሞ።
ጠመዝማዛው የሊማሊሞ መንገድ ልብን ያርዳል፤ ስሜትን ቆንጥጦ ይዛል፤ መንገዱን ለማያውቁ ሹፌሮች ምነው በዚህ መንገድ ባልመጣሁ የሚያስብል አይነት ነው።
ይህን ጭንቅ የኾነ መንገድ ያየች አቀንቃኝም “ሊማሊሞን ዳገት ወጣሁት በዳዴ፣ እንደ ዘጠኝ ወር ልጅ አርግዤህ በሆዴ” ስትል ተቀኝታለታለች።
ሊማሊሞ መንገድ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በደጃዝማች አምሳለ ዘሴ እንደተቆረቆረች ከሚነገርላት ደባርቅ ከተማ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ አካልም ነው።
የአካባቢው የታሪክ አዋቂ በሬ ተፈሪ የሊማሊሞ መንገድ ከመሠራቱ በፊት ነጋ አድራስ ተብለው የሚጠሩ ነጋዴዎች ወደ ቀይ ባሕር የሚወስዷቸውን የተለያዩ የንግድ እቃዎቻቸውን “በመጫኛ” (በጠፍር) አስረው በገደሉ በኩል ያወርዱ እና ያወጡበት እንደነበር ተናግረዋል።
የሊማሊሞ መንገድ በ1920ዎቹ መጨረሻ እንደተሠራ አንስተዋል። መንገዱ ለዘመናት ጥገና ሳይደረግለት እያገለገለ እንደሚገኝም ጠቁመዋል። ሊማሊሞ የሚለውን ስያሜ ያገኘው በወቅቱ መንገዱን ባሠራው ኢንጅነር ስም እንደኾነ ገልጸዋል።
መንገዱ እጅግ አስቸጋሪ ቢኾንም በሹፌሮች ጥንቃቄ በብዛት የመኪና አደጋ እንደማያጋጥም ተናግረዋል። በመንገዱ መካከል የበሬ ሽንጥ፣ አሞራው ስዕል፣ ውልክፊት ተብለው የሚጠሩ ቦታዎች ይገኛሉ።
በ1957ዓ.ም የእንግሊዝ ንግሥት ኤልሳቤጥ ወደ አካባቢው በመምጣት ይህንን ድንቅ ቦታ በማየታቸው ለመታሰቢያነት ንግሥት ማረፊያ እየተባለች የምትጠራ ቤት አካባቢው ላይ እንደተሠራላቸው ተናግረዋል።
በሊማሊሞ ደን ውስጥ ውጨና፣ ውልክፋ እና መሰል በርካታ የሀገር በቀል ተክሎች🌲 መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ለምግብነት የሚያገለግሉ እንደ ቀጋ፣ 🍒እንጆሪ፣ የማርጠቦ ሀረግ እና መሰል ተክሎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።
ሊማሊሞ በውስጡ ነብር፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጅብ፣ ድኩላ፣ ጭላዳ፣ ሚዳቋ፣ ጉሬዛ፣ ዝንጀሮ እና መሰል የዱር እንስሳትን ይዟል።
የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የቱረስት አገልግሎቶች ሙያ ብቃት ማረጋገጥ ቡድን መሪ ሀብቱ ዓለሙ የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ 412 ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ነው፤ ሊማሊሞ መንገድ ከፓርኩ ጋር መከለሉን ተናግረዋል።
ሊማሊሞ መንገድን ይበልጥ የጎብኝዎች መዳረሻ እንዲኾን በአካባቢው ሎጅዎችን በመገንባት ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲሠማሩ ተደርጓል ነው ያሉት።
የሎጅዎች መገንባት ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል። ሊማሊሞ መንገድን ይበልጥ ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑንም አንስተዋል።
#አሚኮዜና#ሊማሊሞ#ቱሪዝም#ኢትዮጵያ🇪🇹 Limalimo #LimalimoGorge #SimienMountains #VisitEthiopia
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ፦









