ከ40 በላይ ኤምባሲዎችን ጨምሮ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተወከሉ ከ70 በላይ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች እና የልማት አጋሮች ከአፍሪካ እጅግ አስደናቂ ባሕላዊ እና መንፈሳዊ ቅርሶች መገኛ በኾነችው በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከሰሞኑ ጉብኝት አድርገዋል።
ይህ ታሪካዊ ጉብኝት በዓለም አቀፍ ደረጃ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የመንከባከብ እና የመጠበቅ የጋራ ቃልኪዳንን በድጋሚ ለማደስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ይህን ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ያዘጋጀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ ከአማራ ክልል መንግሥት፣ ከላሊበላ ከተማ አሥተዳደር እና በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ ከሚንቀሳቀሰው “ዘላቂ ላሊበላ” ፕሮጀክት (Sustainable Lalibela Project) ጋር በመኾን ነው።
ላሊበላ እ.አ.አ በ1978 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈሩት ድንቅ አብያተ ክርስቲያናትን ይዛለች።
ከ800 ዓመታት በፊት (በ13ኛው ክፍለ ዘመን) ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የታነጹት 11ዱ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት፤ ዛሬም ድረስ መላውን ዓለም በአድናቆት የሚጎበኛቸው፣ የጥንታዊ ምህንድስና እና የመንፈሳዊነት ጥልቅ መገለጫዎች መኾናቸውን ዩኔስኮ ጉብኝቱን አስመልክቶ ባወጣው ጽሑፍ ላይ አመልክቷል።
በጉብኝቱ የተሳተፉት ዲፕሎማቶች እንደ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ አማኑኤል እና ቤተ ቅዱስ መርቆሬዎስ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ተመልክተዋል።
ዲፕሎማቶቹ ላሊበላን “ከዚህ ዓለም ስሪት የላቀ እጹብ ድንቅ ጥበብ” ነው ሲሉ መግለጻቸውን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
#ላሊበላ #የኢትዮጵያቅርሶች #ቱሪዝምኢትዮጵያ #ዩኔስኮ #የዓለምቅርስ #ኢትዮጵያ #ታሪክናባህል #Lalibela #UNESCO #WorldHeritage #VisitEthiopia #SustainableLalibela
#ባሕር_ዳር #ሐምሌ02_2018_ዓ_ም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









