የማይባር ሐይቅ – ድብቁ የቱሪዝም ጸጋ

0
11
ሰንሰለታማ ተራሮችን ተንተርሶ ለጥ ካለው ሜዳ ላይ የሰማይ ሰገነትን ዘርግቶ የሚገኘው የማይባር ሐይቅ፣ ድንቅ እና ውብ ተፈጥሮ የተቸረው የጸጋ ባለቤት ነው።
ከተራራው ስር ኾኖ ሲታይ ሰማዩ የሚነካካበት፣ ከርቀት ሲያዩት ደግሞ ለዕይታ የሚማርክ እና መንፈስን የሚያድስ ልዩ ሥፍራም ነው።
የማይባር ሐይቅ ከደሴ ከተማ በ25 ኪሎ ሜትር፣ ከአልቡኮ ወረዳ ዋና ከተማ ሳልመኔ ደግሞ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተንጣሎ ይገኛል።
በደቡብ ወሎ ዞን የአልቡኮ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የባሕል እሴቶች እና የኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ሙሐመድ ካሳሁን እንደገለጹት ሐይቁ 50 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲኾን ጥልቀቱ እስከ 10 ነጥብ 5 ሜትር ይደርሳል።
ከተራራዎች በታች እና ለጥ ያለ ሜዳማ ስፍራ ላይ የሚገኘው የማይባር ሐይቅ የውኃ ቀለም ወደ ሰማያዊነት የሚያደላ ነው።
አካባቢው ውብ የአየር ፀባይ ያለው በመኾኑ ለሽርሽር፣ ለዕይታ እና ልዩ ሐሴትን ለማግኘት ተመራጭ ያደርገዋል።
የአካባቢው ማኅበረሰብ የተመቸውን አየር እየኮመኮመ፣ የተጣሉትን የሚያስታርቅበት፣ ሰላም፣ መተሳሰብ እና መዋደድ እንዲሰፍን የሚያደርግበት የውይይት እና የመምከሪያ ቦታም ነው።
ሐይቁ የውብ አዕዋፍ መኖሪያ ሲኾን፣ በዳርቻዎቹ እና በውኃው ውስጥ እየተዝናኑ ኑሯቸውን ያደረጉ ፍጥረታት አካባቢውን ተጨማሪ ውበት አልብሰውታል።
በውስጡ ቀረሶ እና ሌሎችም የዓሣ ዝርያዎች እንደሚገኙ ቡድን መሪው ገልጸዋል።
ወጣቶች በግል እና በቡድን ተደራጅተው ዓሣ በማውጣት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፤ ይሁን እንጂ የሐይቁ እምቅ የሀብት አቅም በሙሉ ጥቅም ላይ አልዋለም ይላሉ።
ሐይቁን በማልማት ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተለያዩ የማስተዋወቅ ተግባራት እየተከናወኑ መኾኑን የገለጹት ቡድን መሪው፣ ሥራው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ ይበልጥ ለዓለም እንዲተዋወቅ እና የቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን በቅንጅት መሥራት ይጠበቃልም ብለዋል።
በሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here