የአዝማሪው ማሲንቆ፤ የኮበሌው ዋሽንት፤ የሳዱላዎች ድምጽ እና የእናቶች የወፍጮ ላይ እንጉርጉሮ በአንድነት ተዋደው አንጀት የሚበላ ዜማ የሚሠራባት ወሎ የአራቱ ቅኝቶች መፍለቂያ ናት። ትዝታ፣ ባቲ፣ አምባሰል እና አንቺሆዬ ጥንተ መሠረታቸው ወሎ ነው።
የታሪካዊው የወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ደግሞ ለወሎ ኪነ ጥበብ ዕድገት ያበረከተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ጉልህ ነው።
ማሪቱ ለገሰ፣ መሐመድ ይመር (ከመከም)፣ ዳምጤ መኮንን (ባቢ)፣ ዚነት ሙሃባ፣ ጋሽ ፍሥሀ በላይ፣ ያሲን ሙሀመድ እና ሌሎችም አያሌ የሙዚቃ መሳሪያ ተጨዋቾችን እና አርቲስቶችን አበርክቶልናል።

የዛሬ ባለታሪካችን ለቤተሰቦቿ 13ኛ ልጅ ነች። በ12 ወንዶች የተከበበች ብቸኛ የስለት ልጅ ነች። በስስት የምትትታይ በናፍቆት የተገኘች የቤቱ እና የመንደሩ ድምቀት የነበረች።
“ጠይም ደማም ቆንጆ ከሁሉ ተግባቢ የዋሕ እና ተጨዋች ነች” ይሏታል አብሮአደግ ጓደኞቿ።
“ገና ታዳጊ እያለች ወላጅ እናቷን የተመኝ ወልዴን ሥራ ስታግዝ በተመስጦ ታንጎራጉራለች። ቢጠሯት አቤት አትልም፤ በስሜት ጭልጥ ነው የምትለው ይላል” ወንድሟ የሡፍ ሙሀባ የኪነ ጥበብ ጥሪዋ በጠዋቱ እንደነበር ሲያስታውስ። ከጓደኞቿ ጋር ገንቦዋን አዝላ ውኃ ስትቀዳ፤ በጎች ስትጠብቅ አልያም ሠርግ ላይ ስትዘፍን ጨዋታው ይደራል። ከፍ እያለች ስትመጣ ሆጤ፤ ፒያሳ እና ጢጣ ከወንድሟ የሡፍ ሙሀባ ጋር እየሄደች በዓል ታደምቅ ጀመር።
ወላጅ አባቷ ሙሀባ ይመር መዝፈኗን ባይወዱም እናቷ ግን የሕይወት ጥሪዋን ይደግፉ ነበር። በደሴ ከተማ በተለምዶ ቁርቁር “አጎሮጨባ” እየተባለ በሚጠራው የገጠር አካባቢ በ1959 ዓ.ም ነው የተወለደችው። በካቶሊክ እና በቅዳሜ ገበያ ትምህርት ቤቶች እስከ 7ኛ ክፍል የቀለም ትምህርት ተከታትላለች።
በ1980ዎቹ መጀመሪያ የወሎ ላሊበላ ኪነት ቡድን ካሳደጋቸው እና ዝናቸው በመላው ኢትዮጵያ ከናኘ የጥበብ ፈርጦች መካከል አንዷ ናት- ፍልቅልቋ ዚነት ሙሃባ።

ወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን ታዳጊ ድምጻውያንን ከሁሉም የከተማዋ ቀበሌ ሲመለምል ዕድሉ የገጠማት ዚነት በወሎ በኪነት ቡድኑ ከደመቁት የመጀመሪያዋ ነች። የኪነት ቡድኑን ስትቀላቀል ሥራ የጀመረችው በተወዛዋዥነት ነበር።
እንዲያው ከምበል ደፋ፣ ሽሽጌ፣ ነይ ዳማ፣ ቦረና ነው ቤቱ፣ ሆዴ ሽብር ሽብር፣ አንተ ልጅ ናልኝ፣ ያገሬ ልጅ፣ አመል፣ ያለኸው ከማዶ፣ የጠይም አታላይ፣ ምን ይሻላል? የሚሉት እና ሌሎች ዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ሥራዎቿ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ታትመዋል።
ከስቱዲዮ ውጭ በወሎ ላሊበላ አዳራሽ የተቀረጸው “እንዲያው ከምበል ደፋ” አልበሟ የበኩር ሥራዋ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲስ አበባ ውጭ በክፍለ ሀገር የተቀረጸ እና ተወዳጅ ካሴት እና
ታሪካዊ ሥራም እንደኾነ ይነገራል።
አልበሙን ሲዘጋጅ ግጥም እና ዜማ የሠራላት ዳምጤ መኮንን (ባቢ) ነው። የዚነት የመጀመሪያ ካሴቷ “ከምበል ደፋ” ከመለቀቁ በፊት ለሁለት ዓመት ያክል መድረክ ላይ ለተመልካች ይቀርብ እንደነበር ዳምጤ መኮንን ያስታውሳል።

“ዘና ብላ እና ተፈጥራዊ ፍሰቱን ጠብቃ ስለምታዜም ያለምንም የስቱዲዮ ዝግጅት መድረክ ላይ ያቀረበችው ሙዚቃ በቀጥታ ካሴት ኾነ” ይላል።
“በመድረክ ላይ ስምንት ሙዚቃዎችን በአንድ ጊዜ ተጫወተች። አበበ አዲስ የተባለ የጥበብ ሰው እንዴ ባቢ ይሄ ሥራ አንድ ካሴት ይኾናል አለኝ ወሎ ባሕል አምባ መድረክ ላይ በጋሽ ታምሬ ከ”ሞንታርቦ” ላይ በጥሩ ሁኔታ ተቀረጸ” ይላል የሙዚቃ ግጥም እና ዜማ ደራሲው ዳምጤ መኮንን የዚነት የበኩር ሥራ የተሠራበትን አጋጣሚ ሲያስታውስ።
በካሴት ለአድማጭ ከመድረሱ በፊት ገዥ ፍለጋ ለሁለት ዓመት የተንከራተተው የዚነት ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ይፋ ሲኾን ግን በመላው ኢትዮጵያ ተቀባይነት አገኘ። በሽያጭ ደረጃም ክብረወሰኑን ያዘ።
“እንዲያው ከምበል ደፋ” በሚለው ዘፈኗ የጎፈሬው ውበት ገና ከርቀት የሚለይ፤ በእያንዳንዱ እርምጃ ውስጥ ጎፈሬው ከንበል ደፋ የሚልለት፤ የዚነትን ልብ የሰረቀ አንድ ጎበዝ አለ። ታዲያ በጎፈሬው ውበት ተማርካ፣ በመንገድኛነቱ የተሰቃየችው ዚነት በተስረቅራቂ ድምጿ “ከምበል ደፋን” ስትጫወተው ወደር የላትም።
ሌላኛው ሥራዋ “ምን ይሻላል? ” ነው። ለብቻዋ መቋቋምን መፍትሔ ያላገኘችለትን ችግሯን፣ ናፍቆቷን፣ ትዝታዋን ማስታገሻ መፍትሔ ፍለጋ “ምን ይሻላል?” ስትል ምክርን ጠይቃ ነበር። እኛ ደግሞ ዛሬ ዚነትን እንናፍቃለን። ዘፈኖቿን ስናዳምጥ ወደ 70ዎቹ መጨረሻ እና 80ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የኋሊት በትዝታ እንነጉዳለን። ዘመንን እንደ ብራና አይጠቀልሉት ነገር- ምን ይሻላል? እንላለን።
ከጥበብ አበርክቶዋ ባሻገር የተቸገረ ስታይ አንጀቷ የሚንሰፈሰፍ፤ የእጇን ለድሆች በማጉረስ አንዳች ጥሪት ያልነበራት ለጋስ ነበረች። ዚነት ለሰዎች አዛኝ፣ መኮፈስ እና ኩራትን አብዝታ የምትጸየፍ የመልካም ሰብዕና ባለቤትም ነበረች ይላሉ በቅርበት የሚያውቋት ጓደኞቿ።
“ሳትቀባባ የሚያምርባት ፍልቅልቅ፤ ከሁሉ ጋር ተግባቢ አብዝታ መዝናናት የምትወድ እና ሳንጠግባት ያጣናት ነች” ይሏታል የሙያ አጋሮቿ ሙሀመድ ይመር ከመከም እና አዲሡ አሰፋ::

ዚነት ሦስት አልበሞችን አበርክታልን፣ አራተኛውን በማገባደድ ላይ እያለች ሩቅ አስባ ብዙ መሥራት በምትችልበት በለጋ ዕድሜዋ ቅርብ አደረች። ከሙሀመድ ኮይስ ጋር በጥንድ የተጫወቱት ሸጋ የሙዚቃ ሥራ ዛሬም ከነ ሙሉ ወዙ ይደመጣል።
በአጭር ጊዜ ውስጥ የሀገራችንን ኪነ ጥበብ ያደመቀቸው ኮኮብ ከአፈር ውስጥ አረጀች። በዘመን አይሽሬ የሙዚቃ ሥራዎቿ ከመቃብር በላይ በገነነው ስሟ በልባችን ነግሳ በትውልዱ ሁሉ ስትታወስ ትኖራለች።
#አሚኮ #ኪነ_ጥበብ
#ባሕር_ዳር #ነሐሴ_06_2018_ዓ_ም
✍️ በአንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









