መንፈሳዊነት እና ተፈጥሮ የተሳሰሩበት ድንቅ ምድር፦ የማኅበረ ሥላሴ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ።

0
36

 

በምዕራብ ጎንደር ዞን አድማስ ሥር የዘመናት ታሪክ እና ያልተነካ የተፈጥሮ ምስጢር የተሰናሰሉበት፣ የቅድስናው ማዕበል ከተፈጥሮው ለምለም አየር ጋር የተዋሀደበት
አንድ ድንቅ ስፍራ አለ።

ይሄ ስፍራ በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነገሥታቱ አብርሃ ወአጽብሃ በተመሠረተው ጥንታዊው እና ታሪካዊው የማኅበረ ሥላሴ አንድነት ገዳም ስም የሚጠራው የማኅበረ ሥላሴ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ ነው።

ከ19 ሺህ ሄክታር በላይ በኾነ ሰፊ የቆዳ ስፋት ላይ ያረፈው ይህ ጥብቅ ደን በምዕራብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ አሸብርቀው ከሚታዩ የተፈጥሮ ሀብቶች መካከል አንዱ እና ዋነኛው መኾኑን የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራው ኀላፊ ኮማንደር ክንድነው አሰፋ ይናገራሉ።

ይህ ድንቅ የተፈጥሮ ገነት በሦሥት ወረዳዎች እቅፍ ውስጥ ይገኛል፤ በሰሜን፣ በደቡብ እና በምዕራብ በኩል መተማ ወረዳ፣ በምሥራቅ አዳኝ አገር ጫቆ፣ በደቡብ ምዕራብ ቋራ ወረዳ ያዋስኑታል።

የዚህ ስፍራ ልዩ ውበት እና ምስጢር የሚጀምረው ከመልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ ነው። ቦታው በቆላማ የአየር ንብረት ክልል ውስጥ የሚገኝ ነው። ከባሕር ወለል በላይ በአማካይ ከ650 እስከ 1ሺህ 350 ሜትር ከፍታ አለው።

የሙቀት መጠኑ እስከ 40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይደርሳል።

የዚሁ ታሪካዊ ገዳም መነኮሳት የማኅበረሰቡ ፍቅር እና እንክብካቤ ሳይለያቸው ብዝኅ ሃብቱን እንደ ነፍሳቸው ለዘመናት አክብረው ጠብቀው አቆይተውታል።

ይሁን እንጅ የዚህ ጥብቅ ደን ግርማ ሞገስ የነበሩት እንደ ጎሽ እና አንበሳ ያሉ ታላላቅ የእንስሳት ዝርያዎች ዛሬ በመዳከም ላይ ይገኛሉ።

ጫካው አሁንም ሕይወት የሞላበት ሕያው መጠጊያ ነው። በውስጡ ነብር፣ አጋዘን፣ ዝንጀሮ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋ እና ሌሎች የዱር እንስሳት፣ አጥቢዎች እና የአእዋፋት ዝርያዎች በነፃነት ይቦርቁበታል።

ከ26 በላይ የሚኾኑ ልዩ ልዩ የአጥቢ እንስሳት ዝርያዎች፣ ከ100 በላይ የሚደርሱ አእዋፋት ጥብቅ ሥፍራውን መኖሪያ አድርገውታል።

የዚህ ምድር ሃብት በእንስሳቱ ብቻ አያበቃም፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ምህዳራዊ እና ሥነ ሕይወታዊ ፋይዳቸው ከፍተኛ የኾነ ከ100 በላይ የእፅዋት ዝርያዎች ባለቤት መኾኑንም ኮማንደር ክንድነው ይናገራሉ።

ይህ ተፈጥሯዊ ሃብት ለአካባቢው ሕዝብም ትልቅ በረከት ነው፤ የእጣን ዛፉ ለገዳሙ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ከመኾኑ ባሻገር በአካባቢው ለሚኖሩ ወጣቶችም ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጥሯል።

#አሚኮ #የተፈጥሮ_ጥብቅ_ደን#ምዕራብጎንደር_አማራክልል #ኢትዮጵያዊ 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_11_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here