የተራራው ላይ ንጉሥ፣ የኢትዮጵያ ምልክት እንዴት እየተጠበቀ ነው?

0
85
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኘው እና በተፈጥሮ ማራኪነቱ የሚታወቀው የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በተፈጥሮ ቅርስነት ከተመዘገቡ ድንቅ ስፍራዎች አንዱ ነው።
ይህ ፓርክ በዓለም ላይ በሌላ በማንኛውም ስፍራ የማይገኙ ብቸኛ የተፈጥሮ ሃብቶችን በውስጡ የያዘ ሲኾን፣ ከእነዚህም መካከል ዋልያ አይቤክስ ዋነኛው እና የፓርኩ ህያው መገለጫ ነው።
ዋልያ አይቤክስ በዓለም ላይ በኢትዮጵያ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በሰሜን ተራራዎች ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ብቻ የሚገኝ የኢትዮጵያ ምልክት ነው። ዋሊያ ከፍታ ባላቸው ገደላማ እና አቀበታማ ቋጥኞች ላይ የመውረድ እና መውጣት አስደናቂ ተፈጥሯዊ ብቃት አለው።
ይህ ብቸኛ እንስሳ ለሀገራችን በርካታ ጥቅሞች አሉት። ዓለምአቀፍ ጎብኝዎችን በመሳብ እንደሀገር የውጭ ምንዛሬ፣ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ደግሞ የሥራ ዕድል እና የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው ነው።
የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፖርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ የፓርኩ ዋነኛ ምልክት የኾነው ዋልያ በየዘመናቱ የተለያዩ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎችን ሲያስተናግድ መቆየቱን አብራርተዋል። በተለይም በጸጥታ ችግሮች ወቅት በደን ጭፍጨፋ እና በሕገ ወጥ አደን ምክንያት የእንስሳቱ ቁጥር መዋዠቅ ይታይበት ነበር።
ከኮረና ወረርሽኝ እና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከወረርሽኙ መከሰት ጋር ተያይዞ በነበሩ የክትትል መላላቶች እና ተያያዥ ምክንያቶች የዋልያ ቁጥር መቀነስ አጋጥሞ እንደነበርም ይጠቅሳሉ።
በአሁኑ ወቅት በዚህ ብቸኛ እንስሳ ደኅንነት፣ መኖሪያ እና አሁናዊ ቁጥር ዙሪያ በፓርኩ ውስጥ የተቀናጀ ሰፊ የጥበቃ እና የቆጠራ ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ለአሚኮ ገልጸዋል።
አቶ ማሩ እንደገለጹት የዋልያን መጥፋት ከስጋት ለመታደግ በክልል እና በፌዴራል ደረጃ በርካታ የተቀናጁ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የዋልያ የጥበቃ ሥራ ውጤታማ የሚኾነው የአካባቢውን ኅብረተሰብ በተለይም ወጣቶችን ማዕከል ሲያደርግ ነው ያሉት ኀላፊው በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙ ወጣቶችን በማደራጀት እና በፓርክ ጥበቃ ሥራዎች ላይ በማሳተፍ ዘላቂ ጥበቃ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ዋልያ በተፈጥሮው ጸጥታን እና ሰላማዊ አካባቢን የሚወድ እንስሳ ነው። አሁንም ይህንን ተፈጥሯዊ ጸባዩን ታሳቢ ያደረገ የጥበቃ እና የእንክብካቤ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፤ አካባቢው ለዋልያዎቹ ምቹ እና ሰላማዊ እንዲኾን የወጣቶች አደረጃጀት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነውም ብለዋል።
በፓርኩ በመካሄድ ላይ ያለው የተቀናጀ ቆጠራ የእንስሳቱን አሁናዊ ቁጥር፣ የፆታ ስብጥር እንዲሁም የጤንነት ሁኔታ በትክክል ለማወቅ የሚረዳ አስፈላጊ ሂደት ነው ብለዋል የፓርኩ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ።
የቆጠራው ሂደት ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ አጠቃላይ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ምልክት የኾነው ብርቅየ እንስሳ በመረጠው የሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ በነጻነት እና በሰላም ተንቀሳቅሶ እንዲኖር የሚደረገው ጥረት መጠናከር እንዳለበትም
አመላክተዋል። የፓርኩን የዓለም ቅርስነት አስከብሮ ማስቀጠልም የሁሉም ኢትዮጵያውያን በተለይም የአካባቢው ማኅበረሰብ ትልቅ ሀገራዊ ኀላፊነት ስለመኾኑም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በበቃሉ ጎረምስ
(ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሚኮ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here