ባሕር ዳር: መጋቢት 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ከሚገኙ ጥንታዊ እና መንፈሳዊ የሃይማኖት ሥፍራዎች መካካል ደብረ ዕንቁ ማርያም ገዳም ትጠቀሳለች።
ደብረ እንቁ ማርያም በደቡብ ጎንደር ዞን ስማዳ ወረዳ የምትገኝ ተራራ ላይ የተመሠረተች ጥንታዊት እና ታሪካዊት ገዳም ናት። ገዳሟ ከወገዳ ከተማ በግምት 37 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በየኳሳ ቀበሌ ነው የምትገኘው።
የደብረ ዕንቁ ማርያም ገዳም አሥተዳዳሪ አባ ኪዳነ ማርያም ገብረ ጊዮርጊስ ገዳሟ ከኦሪት ዘመን ጀምሮ ታቦተ ጽዮን ተብላ በድንኳን አገልግሎት ይሰጥባት እንደነበር ታሪክ ከትቧታል ብለዋል።
ከዘመናት በፊት የመቃጠል እና የመፈራረስ ችግር ገጥሟት እንደነበርም ታሪኳ እንደሚያትት አንስተዋል። በኋላም በሐዲስ ኪዳን እንደገና ተመልሳ በአቡነ ፊሊጶስ አማካኝነት ቤተ ክስርቲያኗ እንደተመሠረተች ነው የተናገሩት።
በአጼ አምደጽዮን ዘመነ መንግሥትም በቅዱሱ አባት በአቡነ ፊሊጶስ እንደተገደመች ገልጸዋል። የአባቶች እና የእናቶች መነኮሳት ገዳም አድርገዋት እንደነበርም ገልጸዋል።
ወለተ ጴጥሮስ መጀመሪያ ገዳም የገባችበት እና 99 መነኩሳት ያገለገሉበት ቦታ ናትም ብለዋል። ክብረ በዓሏም በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት ይከበራል ነው ያሉት።
የገዳሟ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ አስገራሚ፣ አንድ መውጫ እና መግቢያ በር ብቻ ያላት መኾኗ ትኩረትን ትስባለች ብለዋል አሥተዳዳሪው።
ግማደ መስቀሉ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ከመሄዱ በፊት መስቀሉ በጉዞ ላይ እያለ ከዚች ቦታ ላይ ለስምንት ቀናት አርፏል። በዚህም ዳግማዊ ግሸን ደብረ ከርቤ በማለት ትጠራለች ነው ያሉት።
በተለያዩ የደን ዛፎች የተከበበችው ደብረ ዕንቁ ማርያም ገዳም በርካታ ቅርሶችን አቅፋ ይዛለች።
ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት እንደሚገኙም አሥተዳዳሪው ጠቅሰዋል።
የስማዳ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ደስታው ይንገስ ገዳሟን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በገዳሟ የሚገኙ ቅርሶችን ለመጠበቅ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ለቅርሱ ተገቢውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ለማድረግ የጸጥታ ችግር ፈታኝ እንደኾነባቸውም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









