የክረምቱ ደመና ሰማዩን ሲጋርድ፣ ነፋሱ እና ዝናቡ ቅዝቃዜውን ይዘው ሲመጡ በብዙዎች ኢትዮጵያውያን መኖሪያ ቤት ውስጥ ሌላ ዓይነት ሙቀት ይፈጠራል። ይኸውም በእሳት ላይ የሚጠበሰው የበቆሎ እሸት ሽታ እና በጋለ እሳት ዙሪያ የሚሠበሠበው ቤተሰብ የሚፈጥረው ድምቀት ነው።
የበቆሎ እሸት ለኢትዮጵያውያን ምግብ ብቻ ሳይኾን የክረምቱ ቅዝቃዜ ማሸነፊያ፣ የፍቅር፣ የትስስር እና የጋራ ውይይት ታላቅ ማኅበራዊ መድረክ ነው።
የፍቅር እና የተካፍሎ የመብላት ማሳያም ነው። በክረምት ወቅት በቆሎን በቤት ውስጥ ጠብሶ መመገብ ረጅም ዘመናት የተሻገረ ድንቅ ባሕል ነው። እሸቱ በእሳት ላይ ሲጠበስ የሚወጣው ሙቀት ቤቱን አሙቆ ለቤተሰቡ ልዩ ድባብ ይፈጥራል።
ከሁሉም በላይ ግን አንድ የተጠበሰ በቆሎ ተቆርጦ ለሦሥት እና ለአራት ሰዎች መከፋፈሉ ወላጆቻችን አስተላልፈውልን ያለፉትን “ተካፍሎ መብላት” የሚል የመደጋገፍ እና የፍቅር እሴት በግልጽ የሚያሳይ ነው።
የቤተሰብ በእሳት ዙሪያ መሠባሠብ በጋራ ይበልጥ እንዲቀራረቡ እና አብሮነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያደርጋቸዋል።
በቆሎ እሸት ከኢትዮጵያውያን የቡና ሥነ-ሥርዓት ጋር ያለው ቁርኝትም ልዩ ነው። ቡናው ተፈልቶ፣ የዕጣኑ ጭስ ከበቆሎው ሽታ ጋር ሲቀላቀል የመኖሪያ ቤቱ አየር ሙሉ በሙሉ ይለወጣል።
በቆሎ እየተበላ የሚጠጣው የክረምት ቡና፣ ቤተሰብ ስለ ውሎው፣ ስለ ኑሮው እና ስለ ማኅበራዊ ጉዳዮች በግልጽ እና በነፃነት የሚወያይበትን ዕድልም ይፈጥራል።
ይህ አጋጣሚ የወላጆች እና የልጆች ግንኙነት የሚጠናከርበት፣ የዕለት ተዕለት ውሎ የሚጋራበት እና የትውልድ ክፍተትን ለማጥበብ የሚያግዝ መድረክ ኾኖም ያገለግላል።
የበቆሎ እሸት ማኅበራዊ ፋይዳው ብቻ ሳይኾን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውም የጎላ ነው። ከአምራች አርሶ አደሮች ጀምሮ እሸቱን ወደ ከተማ የሚያጓጉዙ፣ በየጎዳናው እና በየሰፈሩ በቆሎን አብስለው የሚሸጡ በርካታ ዜጎች በክረምት ወቅት የገቢ ምንጭ ያገኛሉ።
የበቆሎ እሸት ኪስን በማይጎዳ፣ አቅምን ያገናዘበ እና ማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ገዝቶ ቤተሰቡን የሚያስተናግድበት ማዕድ በመኾኑ የበርካቶች ደጋፊ ነው።
እንዲያው በጥቅል የበቆሎ እሸት በኢትዮጵያውያን የክረምት ወቅት ውስጥ የምግብ ፍላጎትን ከማሟላት ባለፈ ትልቅ ትርጉም አለው። ቅዝቃዜውን በሙቀቱ፣ ረሃቡን በማስታገሱ፣ ብቸኝነቱን ደግሞ በፍቅር እና ተካፍሎ በመብላት ባሕሉ የሚሸፍን ድንቅ የማኅበራዊ ሕይወት ነው።
ዘጋቢ፦ ፍሬሕይወት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









