ከራስ ደጀን ግርጌ ያለው ድንቅ ሥፍራ

0
41

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ሠንሠለታማ ተራራዎች፣ ሀገር በቀል ተክሎች እና የምድሩ ልምላሜ ድንቅ ውበትን ሰጥቶታት። የብርቅዬ እንስሳትም ለስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ውበትን አላብሰውታል።

በግርማ ሞገሱ ከተቀመጠው ከራስ ደጀን ተራራ ሥር በቅርብ ርቀት የሚገኘው የጥዑም ዜማ ደራሲው አባት ደብረ ሃዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ለአካባቢው ተጨማሪ ውበትን አጎናጽፎታል።

የደብረ ሃዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም የልማት አሥተባባሪ አባ ወልደ ሰንበት ወልደ ያሬድ ገዳሙ በ545 ዓ.ም በዜማ ደራሲው በቅዱስ ያሬድ አማካኝነት የተመሠረተ ጥንታዊ ገዳም መኾኑን ተናግረዋል።
ቅዱስ ያሬድ በገዳሙ ለረጅም ጊዜ እንደኖሩበት ገልጸዋል። አንድነት ገዳሙ ከ1 ሺህ 500 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳለው ነው የተናገሩት።

በገዳሙ ሀገር በቀል ተክሎች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት እና ጥብቅ ደኑ ተጠብቆ እንደሚገኝም አንስተዋል። የጥብቅ ደኑ መጠበቅ እና አካባቢያዊ አቀማመጡ በተለይም በረዶ የማይለይበት ቦታ መኾኑ ለቱሪዝም ተደራሽነት ማራኪ መኾኑን ገልጸዋል።

የቅዱስ ያሬድን ሕያውነት ለመመስከር፣ የዜማ ድርሰቶቹን ለማስቀጠል፣ ለዓለም ያበረከቱትን የዜማ ድርሰቶቻቸውን ለመዘከር፣ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ሰፊ እና ዓለማቀፋዊ ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት ንድፍ በማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከቤተክርስቲያኑ ባሻገር በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተለያዩ ማዕከላት እንደሚገነቡም ጠቁመዋል።

የቤተ ክርስቲያኑ መገንባት በአካባቢው የሥራ ዕድል የሚፈጥር፣ ለወጣቶች ሃይማኖታዊ እና ዘመናዊ ዕውቀት የሚፈጥር ነው ብለዋል። ሁሉም የተሰጠውን ጸጋ እንዲጠቀም የሚያስችል መኾኑንም ተናግረዋል።

የበየዳ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኀላፊ አብርሐም ሞገስ ገዳሙ ለአካባቢው በቱሪዝም መስህብነት እያገለገለ መኾኑን አንስተዋል።

ለስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ብዝኀ ሕይወት መጠበቅ ሚናው የጎላ መኾኑንም ተናግረዋል።

የሚገነባው ቤተ ክርስቲያን በውስጡ የጤና ተቋማትን፣ ሃይማኖታዊ እና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን፣ የጎብኝዎች ማረፊያ፣ የዕደ ጥበብ ሥልጠና መስጫ እና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ጨምሮ እንደሚገነባም ተናግረዋል።

ይህም ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር እና ለማኅበረሰቡ የጤና አገልግሎት እንደሚሰጥ አንስተዋል። ለሳይንስ እና ምርምር ሥራዎች ጉልህ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

የቅዱስ ያሬድ ሥራዎችን ለዓለም እንደሚያሳውቅም ጠቁመዋል። ዓለማቀፋዊ ቤተ ክርስቲያኑ በ300 ቢሊዮን ብር በጀት እንደሚገነባም ተናግረዋል።

ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here