በጋዲሎ ሜዳ የሚገኙት ምስጢራዊ ሐውልቶች !

0
19
ደብረ ብርሃን፦ 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከአጣዬ ከተማ ተነስተው ወደ መሀል ሜዳ በሚወስደው አስፓልት መንገድ ላይ 21 ኪሎ ሜትሮችን ሲጓዙ የመሀል ወንዝ ቀበሌ ላይ ታሪካዊው የጋዲሎ ሜዳ ይገኛል፡፡
ይህን 32 ነጥብ 5 ሄክታር ሜዳ አቋርጠው ጥቂት እንደተጓዙ አንድ ያልተለመደ እና አስገራሚ እይታ የዓይንዎን ትኩረት ይስባል። እርስ በእርስ የተጠጋጉ ጥንታዊ ድንጋዮች በዝምታ ቆመው ያገኟቸዋል። እነዚህ ድንጋዮች ዝምተኞች ቢኾኑም በውስጣቸው ግን የዘመናትን ታሪክ አፍነው ይዘዋል።
የኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ ታለጌታ ለጥይበሉ ለአሚኮ እንደተናገሩት በዚህ ስፍራ በአሁኑ ሰዓት 35 ድንጋዮች በግልጽ ቆመው ይገኛሉ ብለዋል። ይሁን እንጂ በአካባቢው በጥቅሉ 62 የሚደርሱ የሰው ምስል ያላቸው ድንጋዮች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
ወደ ድንጋዮቹ ጠጋ ብለው ሲመለከቱ በጥንታውያኑ እጆች በጥበብ የተቀረጹ የፊት ገጽታዎችን ያስተውላሉ። ዓይን፣ አፍንጫ፣ ጆሮ፣ አፍ እና የጾታ መለያ ጭምር በግልጽ ማየት ይቻላል። ምንም እንኳ እስካሁን ድረስ ሳይንሳዊ የአርኪኦሎጂ ምርምር እና ጥናት ባይደረግላቸውም ነው ያሉት ቡድን መሪው።
የጥንቱ ማኅበረሰብ ምን ያህል የላቀ የፈጠራ ጥበብ እና ዕደ-ጥበብ እንደነበረው ለመገመት ግን አያዳግትም ነው ያሉት።
ከአካባቢው ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው አፈ ታሪክ እንደሚያስረዳው በጥንት ዘመን ሙሽሮች እና ሚዜዎቻቸው ከመጥቆሪያ ተነስተው እየጨፈሩ ወደ መሀል ወንዝ ይጓዛሉ። ታዲያ በጉዟቸው ላይ በአንድ ገበሬ ሰብል ላይ ሆ እያሉ እየረገጡ ሲያልፉ ባለቤቱ ሰብሌን አታውድሙብኝ፣ ተመለሱ እያለ ይማጸናቸዋል። ሙሽሮቹ ግን በትዕቢት እምቢ አሉት። በዚህ የተበሳጨው ገበሬም በቆማችሁበት ድንጋይ ያድርጋችሁ! ሲል ረገማቸው።
በዚያው ቅጽበትም እልልታው እና ጭፈራው ቆመ፤ ሙሽሮቹም ድንጋይ ኾነው ቀሩ፤ ከዚያም ስያሜው “የሙሽራ ድንጋይ” ተብሎ ቀረ እየተባለ እንደሚነገር ገልጸዋል፡፡
ይህ አፈ-ታሪክ ዛሬም ድረስ ለቦታው ተጨማሪ ምስጢራዊ ውበትን እና የቱሪስት መስህብነትን የሰጠ ቅርስ እንደኾነ ተናግረዋል። በወረዳው በመንተኬ ሸረፋ ቀበሌ የተገኙ ተመሳሳይ አርኪኦሎጂካዊ ድንጋዮች በዘመኑ የነበረውን የኪነ ሕንጻ ጥበብ ማሳያ መሆናቸውን የሚናገሩት ቡድን መሪው ይህንን ታሪካዊ ሀብት ጠብቆ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ ግን ዛሬ ላይ ትልቅ ፈተና ገጥሞታል ብለዋል።
ከጠቅላላው ቅርሶች መካከል 16ቱ በአሁኑ ወቅት ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው በመኾኑ አስቸኳይ የጥገና እንዲሁም የእንክብካቤ ድጋፍ እንደሚሹም ተናግረዋል፡፡
ከሙሽራ ድንጋይ በተጨማሪ በቅርቡ በመንተኬ ሸረፋ ቀበሌ የተገኙ አዳዲስ ተመሳሳይ የሰው ቅርጽ ያላቸው ድንጋዮች እና መካነ መቃብሮች፣ አካባቢው ገና ያልተገለጠ እና ያልተጠና ታሪክ እንዳለው ማሳያ መኾኑን አቶ ታለጌታ ገልጸዋል።
በመሆኑም ይህ ስፍራ የቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎችን እና የአርኪኦሎጂ ተመራማሪዎችን የሚሻ በመኾኑ ተጨማሪ ጥናት እንዲያደርጉበት ጥሪም አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ ፡- ገንዘብ ታደሰ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here