ባሕር ዳር: ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አሥተባባሪነት በባሕር ዳር ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ሙዚየም ግንባታ አፈጻጸም 27 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ሙዚየሙ በ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ወጭ በባሕር ዳር ከተማ በአጼ ቴዎድሮስ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ዓባይ ማዶ አየር ጤና በሚባል አካባቢ እየተገነባ እንደሚገኝ የተናገሩት የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቅርስ ጥገና ባለሙያው ጥጋቡ አዳፍሬ ናቸው።
መስከረም 2015 ዓ.ም ጅማሮውን ያደረገው ይህ ሙዚየም ባለ አራት ወለል ኾኖ እንደሚገነባ ነው የተናገሩት። ይህ የባሕል ሙዚየም፣ የክልሉ የሕዝብ መገለጫ የኾኑ የሁሉም ብሔረሰቦች ልዩ ልዩ ቅርሶችን በዘመናዊ ሥርዓት አካቶ ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ እና ለዓለም ለማስተዋወቅ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የግንባታ ሥራው በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመውት የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ በተደረገው ጥረት በተሻለ የዕድገት ሂደት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ሙዚየሙን በቀጣዩ 2019 ዓ.ም ላይ ሙሉ በሙሉ አጠናቅቆ ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝም አቶ ጥጋቡ አረጋግጠዋል።
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለክልሉ የቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃትን ከመፍጠሩም በላይ ባሕር ዳር ከተማን ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ እንደሚያደርጋት ነው የጠቆሙት።
#አሚኮ_ዜና #የአማራ_ብሔራዊ_ሙዚየም #ባሕር_ዳር #ቱሪዝም #ኢትዮጵያ 🇪🇹
በእሱባለው ብዙአየሁ (በአሚኮ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









