“የበረሃዋ ንግሥት የሥልጣኔ በር አልዩ አምባ”

0
76
“ጠላት መጣ መሰል ተንጫጩ ወፎቹ ጀግኖች ይጠሩልን አልዩ አምባዎቹ” ተብሎ የተገጠመላት በ1260 ዓ.ም አካባቢ እንደተቆረቆረች የሚነገርላት ጥንታዊቷ አልዩ አምባ ከተማ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በአንኮበር ወረዳ ትገኛለች።
ታሪካዊቷ አልዩ አምባ ከተማ ስያሜውን ያገኘችው በአካባቢው ታዋቂ ነጋዴ በነበሩ “አልየ” ከሚባሉ ግለሰብ ነው።
የአንኮበር ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃ እና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ ዮሐንስ ንጋቱ በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከተማዋ የቆላውን እና የደጋውን ማኅበረሰብ ከማገናኘት ባሻገር የኢትዮጵያን ማዕከል ከቀይ ባሕር ወደብ ጋር ያገናኘች ታላቅ የንግድ መድረክ ናት ይላሉ።
የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በድሮ ጊዜም ኾነ አሁን በአንድነት የሚገበያዩባት ይህች ከተማ ዙሪያውን በተፈጥሮ ግንብ እና በድንጋይ የተከበበች ልዩ አምባ ነች። በዚህም “ትንሿ ሐረር” እየተባለች ትጠራለች ነው ያሉት።
​
ጥንታዊቷ ከተማ በወቅቱ አራት መግቢያ እና መውጫ በሮች ነበሯት። ጨኖ በር እና አዋሽ በር ከውጭ በተለይም ከጅቡቲ፣ ከዘይላ እና ከሌሎችም ወደቦች የሚመጡ ነጋዴዎች እና ሸቀጦች የሚገቡበት የመግቢያ በሮች ነበሩ።
ምንጃር በር እና አንኮበር በር ደግሞ በግብይት ሂደቱ ሕጋዊ ማጣሪያ ካለፉ በኋላ ሸቀጦች ከማዕከላዊ ገበያ ወደ ሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚወጡባቸው መውጫ መንገዶች ነበሩ።
​በወቅቱ የረጅም ርቀት የሲራራ ንግድ የተከናወነባት እና በርካታ ግመሎች ለገበያ መጓጓዣ ያገለገሉባት ናት። አልዩ አምባ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው የጉምሩክ ቀረጥ ማዕከል በመኾንም አገልግላለች።
በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነው የቀረጥ ውል የተፈረመው በአልዩ አምባ ገበያ መሠረት ነው። በአጼ ምኒልክ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረጥ መሥሪያ ቤት ሲከፈት በአልዩ አምባ የጉምሩክ ጽሕፈት ቤት ሥራውን እንዲጀምር ተደርጎ ነበር።
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በምጽዋ እና በአዱሊስ ወደቦች በኩል የሚገቡ እቃዎች የሚስተናገዱባትም ነበረች። የተሠበሠቡ የቀረጥ ደረሰኞች እና መዛግብት የዚህ ታሪክ ሕያው ምስክሮች ናቸው።
በታሪካዊቷ ከተማ ዛሬም ድረስ የቆላው ማኅበረሰብ እንስሳትን፣ አትክልቶችን እና የባሕል ምርቶችን ወደ ደጋው ሲወስድ፤ የደጋው ሕዝብ የጥራጥሬ ምርቶችን ወደ ቆላው በማምጣት ይሸጣል ይለውጣል ነው ያሉት።
​​በቴክኖሎጂም ታሪካዊ ቀዳሚነት ያላት አልዩ አምባ ስልክ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከቤተመንግሥት እስከ አልዩ አምባ ድረስ መስመር ተዘርግቶ ንግድ የሚመራበት እና መረጃ የሚለዋወጥበት ቦታ ነበረች። ዛሬም ድረስ ስልክ ተተክሎበት በነበረው አካባቢ “ስልክ አምባ” የሚባል መጠሪያ ያለው ሰፈር ይገኛል።
ከተማዋ የኢኮኖሚ መገናኛ ብቻ ሳይኾን የአፋር እና የአማራ ማኀበረሰቦች በጋብቻ እና በባሕል ተሳስረው፣ በአንድ ድር የሚኖሩባት የሰላም፣ የፍቅር እና የአብሮነት ምሳሌ ናት ይላሉ።
​ከተማዋ ከአዲስ አበባ በ187 ኪሎ ሜትር፣ ከደብረ ብርሃን ደግሞ በ57 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች። ይችን ታሪካዊ ከተማ የማስተዋወቅ ሥራ መሠራቱን የገለጹት ቡድን መሪው ከገቢዎች ሚኒስቴር እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጉምሩክ ከተማነቷን እና የቀድሞ ገናና ታሪኳን ዳግም ለማደስ እና ለማስታወስ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተመላክቷል።
✍️ዘጋቢ:-ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here