ሃይማኖታዊ ሥርዓት፣ ታሪክ እና ማኅበራዊ ትስስር የሚደምቁበት ዓመታዊው የጥቅምት ሥላሴ ባሕላዊ ገበያ።

0
131

 

በየዓመቱ ጥቅምት 7 ቀን በሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ (ከአዴት ከተማ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ) በሚገኘው የታሪካዊው የጺማ ደብረ ምኅረት አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ገዳም የሚከበረው የጥቅምት ሥላሴ በዓል ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን ከባሕላዊ ገበያ ጋር አጣጥሞ እና ልዩ ሁነትን ይዞ ነው።

በተለያዩ ጊዜ የነበሩ የገዳሙ አሥተዳዳሪዎች ለተለያዩ መንግሥታዊ የሚዲያ ተቋማት የሰጧቸው መረጃዎች እንደሚያስረዱት የዲማ ደብረ ምኅረት አቡነ ዘርዓ ቡሩክ ገዳም በ16ኛው ክፍለ ዘመን መመስረቱን ተከትሎ ከሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ባሻገር በጊዜ ሂደት ከበዓሉ ትይዩ በዓመት አንድ ጊዜ የሚውል ባሕላዊ ገበያ መኖሩን ያስረዳሉ። ቀደም ባለው ጊዜ ለጸበል ወደ ገዳሙ የሚሄዱ የሃይማኖቱ ተከታዮች የተረፋቸውን ስንቅ እና ሲገለገሉባቸው የነበሩ የጋማ ከብቶችን በስጦታ የመለዋወጥ እና የመሻሻጥ ልማድ ባሕላዊ ገበያው እንዲጀመር ምክንያት መኾናቸውንም መረጃዎች ያመላክታሉ።

በገበያው ላይ ባሕላዊ እና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው ቁሳቁሶች፣ የጋማ ከብቶች ማጌጫዎች፣ አልባሳት፣ የግብርና መሣሪያዎች፣ ጠገራ ብርን ጨምሮ የቀደሙ መገበያያ ሳንቲሞች፣ ብራና፣ የብዕር ቀለሞች፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ የጋማ ከብቶች እንዲሁም ባሕላዊ መጠጦች ለሽያጭ ይቀርባሉ።

ገበያው ላይ ለሚታደሙ እንግዶችም እዚያው ምግብ እና ባሕላዊ መጠጥ ተዘጋጅቶ የሚሸኙበት ሁኔታ የሁነቱ ልዩ መገለጫ ነው። በበዓሉ ዕለት በዓይነቱ ልዩ የኾነ የፈረስ ግልቢያ ውድድርም ይካሄዳል።

በ18ኛው እና 19ኛው ክፍለ ዘመን ከአረብ ሀገራት ጭምር ታዳሚዎች ይሳተፉበት የነበረው ይህ ገበያ ከኤርትራ፣ ከአዊ ዞን፣ ከዋሸራ፣ ከቋሪት፣ ከደጋ ዳሞት፣ ከእስቴ እና ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች ማኅበረሰቡ በእግሩ ጭምር እየተጓዘ የሚታደምበት ነበር። አሁን ላይም የሚታደሙት በርካቶች ናቸው።

ሁነቱ የሰዎች መገናኛ፣ የኅብረተሰብ ውይይት ማድረጊያ፣ መጠያየቂያ እና የተጣሉ አካባቢዎች የሚታረቁበት ታላቅ ማኅበራዊ መድረክም ነው።

የሰሜን ጎጃም ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ባንቲገኝ ስሜነህ በሀገር እና በክልል ደረጃ በቅርስነት የተመዘገበው ይህ ባሕላዊ ገበያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ተቀዛቅዞ የቆየ ቢኾንም ዘንድሮ ካለፋት ጥቂት ዓመታት በተሻለ ነባር ይዘቱን ጠብቆ እንዲከበር የባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ መዋቅሩ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመተባበር በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ሢሠራ መቆየቱን ተናግረዋል።

የጽዳት ዘመቻ እና አካባቢውን የማስዋብ ሥራ ቀደም ብሎ መሠራቱንም አስታውሰዋል።

በዛሬው ዕለትም የጥቅምት ሥላሴ ሃይማኖታዊ በዓል በመከበር ላይ እንደሚገኝ፣ ባሕላዊ የገበያ ሥርዓቱ እና ሌሎች ማኅበራዊ ሁነቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

ባሕላዊ ገበያው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚውል እና ባሕላዊ ይዘት ያላቸው ቁሳቁሶች የሚሸጡበት፣ ጎን ለጎንም ልዩ ልዩ ሁነቶች የሚከናወኑበት በመኾኑ ከሌሎች ገበያዎች ልዩ እንደሚያደርገውም ተናግረዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_07_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here