🌊 ታላቁ የዓባይ ወንዝ ልክ እንደ ትኩስ ወተት ወደ ላይ እየገነፈለ ነጭ አረፋ ሲፈጥር አይተው ያውቃሉ?

0
66

 

በተፈጥሮ ድንቅ እጆች የተሳለችው ኢትዮጵያ በውስጧ ከያዘቻቸው ገጸበረከቶች መካከል ዓባይ ወንዝ አንዱ ነው። ዓባይ እግረ ረጅም ነውና ከእናቱ ማሕፀን ከወጣ ጀምሮ በተጓዘባቸው አካባቢዎች ኹሉ በሚያሳየው ግብር፣ ለሰዎች በሚሰጠው ስሜት እና በሌሎች ምክንያቶች የተለያየ ስያሜ ይሰጠዋል። ‘ወተት ዓባይ’ የሚለው መጠሪያም የዚሁ ማሳያ ነው።

ወተት ዓባይ በአማራ ክልል ሰሜን ጎጃም ዞን በአቸፈርና ሜጫ ወረዳዎች አዋሳኝ የቢኮሎ ታዳጊ ከተማ ጠርዝ ላይ ይገኛል። በአካባቢው በሠፊው የሚነገረው አፈታሪክ እንደሚያስረዳው ቀዳማዊ አፄ ኀይለሥላሤ በአንድ ወቅት በዚህ አካባቢ ሲጓዙ የዓባይ ወንዝ በከፍተኛ ኀይልና ወጀብ ሲገማሸር ይመለከታሉ። ልክ እየፈላ እንዳለ ወተት ከውኃው ጠርዝ አልፎ ሲገነፍልና ነጭ አረፋ ሲሠል ተመልክተውም በመገረም “ወተት ዓባይ” እንዳሉት ይነገራል። በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢው ማኅበረሰብ ከንጉሡ ቀደም ብሎ ስያሜውን ይገለገልበት እንደነበረም ይነገራል።

🏞️ ወተት ዓባይ ተራ ወንዝ ሳይኾን የጀማ ወንዝ፣ የቆጋ ወንዝ እና ታላቁ ዓባይ (ግልገል ዓባይ) ወንዝ የሚገናኙበት ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው። ከአራቱ ዋና ዋና የዓባይ ገባሮች አንዱ የኾነው የአሻር ወንዝም ወደ ዓባይ የሚቀላቀለው ከዚሁ ከወተት ዓባይ (ቢኮሎ ዓባይ) ታዳጊ ከተማ ብዙም ሳይርቅ ነው። አካባቢው በለምለም እፅዋትና በወፎች ጫጫታ የተከበበ በመኾኑ ለሪዞርት ግንባታና ለጎብኚዎች ተመራጭ ነው። ለማኅበረሰቡም ያለው ግልጋሎት ዘርፈ ብዙ ነው።

📚 ይህ ስፍራ በተፈጥሮ ውበቱ የተማረኩ ሰዎችን ብቻ ሳይኾን የማኅበራዊ ሳይንስ ተመራማሪዎችንም ትኩረት የሳበ ነው።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ የኾኑት አብረሃም ገነት (ዶ.ር) ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ በሠሩት “በኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ባሕላዊ ጠቀሜታ” (Cultural Significance of River Abay in Ethiopia) የተሰኘው ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ የወተት ዓባይን ማኅበረሰብዓዊ እሴት በጥልቀት ፈትሸውታል። በቢኮሎ ዓባይ ታዳጊ ከተማና በዙሪያው ባሉ የገጠር መንደሮች የሚኖረው ማኅበረሰብ ዓባይን እንደ ተራ ውኃ እንደማይመለከተውም ገልጸዋል። ወንዙ በተፈጥሯዊ ውበቱ የጎብኚ መዳረሻ ከመኾን ባለፈ ከባሕላዊ እምነቶች፣ ከረቂቅ መንፈሳዊ ኀይሎች እና ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የተሳሰረ ህያው ተምሳሌትነት ያለው መኾኑንም አንስተዋል።

📖ታዋቂው የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ ተክለጻድቅ መኩሪያ ደግሞ “የኢትዮጵያ ታሪክ፦ ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ቀዳማዊ ኀይለሥላሤ” በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ሾለ ኢትዮጵያ ወንዞችና ተፈጥሮ አቀማመጥ ሲያብራሩ ኢትዮጵያ ወንዞቿ እርስ በርስ የሚጋጩባትና ተራሮቿ በምናብ የሚናገሩባት ምድር ናት ይላሉ። ይህም ወተት ዓባይ እና ሌሎችም ወንዞች ተጋጭተውና ተስማምተው በመዋሐድ ነጭ ወተት የሚመስል ውበት ያለው አረፍ የሚፈጥሩበት ሁኔታ መኖር ህያው ምስክር ነው።

📲 እናንተስ ይህንን በጥናትና በታሪክ የተደገፈ ድንቅ የተፈጥሮና የባሕል መገናኛ ቦታ ጎብኝታችሁ ታውቃላችሁ? አስተያየታችሁን በኮሜንት አጋሩን👇

#የመደመር_መንግሥት!

#ወተትዓባይ#ቱሪዝምኢትዮጵያ
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_22_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here