በጥቅምት የሚደምቀው የዋልያዎቹ መንደር

0
109
🌟
🇪🇹የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኝ በዩኔስኮ የተመዘገበ ድንቅ የተፈጥሮ ጸጋ ነው። ከ412 ስኩየር ኪሎ ሜትር በላይ ስፋት ባለው ሰፊ መሬቱ ላይ የተዘረጋው ይህ ፓርክ፤ ሰማይ ጠቀስ የኾኑ እና ግርማ ሞገስን የተላበሱ ተራራዎችን፤ ጥልቅ ጉድጓዶችን እና ሰፊ ጠፍጣፋ መሬቶችን በዕቅፉ ይዟል።
በውስጡም ከዓለማችን በብቸኝነት በኢትዮጵያ የሚገኘው ዋልያን ጨምሮ ቀይ ቀበሮ እና ድኩላን የመሳሰሉ ብርቅዬ እንስሳትን ይዟል። ከ1 ሺህ 200 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎችንም የያዘ ውብ ተፈጥሮም ነው።
በጥቅምት እና በኅዳር ወራት የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በወርቃማ ቀለማት ከሰማያዊ ጸዓዳ ሰማይ ጋር ተዳምሮ እጅግ ማራኪ ውበትን ይላበሳል። የዚህ ወቅት የአየር ጸባይ እጅግ ሰላማዊ እና ለጉዞ ምቹ በመኾኑ አረንጓዴ ለምለሙ የተፈጥሮ ጸጋ በደማቅ ሁኔታ ያንጸባርቃል።
በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት ውብ ፏፏቴዎች፤ በተለይም በዓለም በርዝመቱ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የሚነገርለት ባለግርማው ጂንባር ፏፏቴ በዚህ ወቅት በኃይል እና በድምቀት እየፈሰሰ ፓርኩን ልዩ ውበት ያላብሰዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጀምሮ በተከሰቱ ተግዳሮቶች መቀዛቀዝ ገጥሞት የነበረ ቢኾንም አሁን ላይ ተስፋዎች ታይተውበታል።
የብሔራዊ ፓርኩ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማሩ ቢያድግልኝ ከፌዴራል እስከ ክልል ካሉ አካላት ጋር በመቀናጀት ለፓርኩ ልማት ጠንካራ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ገልጸዋል። በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የቱሪስት መተላለፊያ መንገዶችን የማስፋፋት፣ የደኅንነት እና የጸጥታ ሁኔታዎችን የማስተካከል ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል።
ፓርኩን ለጎብኝዎች ሳቢ የማድረግ እና በውስጡ ያሉትን ሃብቶች የመጠበቅ ተግባር በቅንጅት እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ጎብኝዎች ይህን ድንቅ የዓለም ሀብት መጥተው እንድጎበኙም መልዕክት አስተላልፈዋል።
✍️ ዘጋቢ፦ ማማሩ አጃነው (ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሚኮ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here