የጥንታዊ ቅርሶች ማሕደር- አቡነ እንድርያስ ገዳም

0
69

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቡነ እንድርያስ ገዳም በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ በጣራ ገዳም ቀበሌ ይገኛል።

ከአዲስ ዘመን ከተማ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት፣ ከባሕር ዳር-ጎንደር ከሚወስደው መንገድ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ አራት ኪሎ ሜትር ርቀት ገባ ብሎ ነው ያለው።

ለ440 ዓመታት የኦሪት መሥዋዕት ሲሠዋበት እንደነበር ከሊቦ ከምከም ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ገዳሙ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ889 ዓ.ዓ የተመሠረተ ነው። በተለምዶ አቡነ እንድርያስ ዋሻ በመባል ይታወቃል፡፡ በዋሻው ውስጥ ለውስጥም እስከ 16 ኪሎ ሜትር የሚረዝም መንገድ እንዳለውም ይነገራል፡፡

በዘመነ ኦሪት የነበረ ገንዳ፣ የዜና ማርያም መጸለያ ገንዳ፣ በእንጨት የተሠራ የኦሪት መሠዊያ፣ አጼ ዘርዓያዕቆብ ለገዳሙ ከሰጧቸው 6 ነጋሪቶች መካከል ሁለቱ በስፍራው ይገኛሉ።

ብዛት ያላቸው ቅርጻቸውን ያልለቀቁ የቅዱሳን አስከሬኖች እና አጽሞች ሕያው መስለው ይገኛሉ። በውስጡ ጥንታዊነትን የሚገልጹ ቅርጻ ቅርጾች እና አምዶች፣ ድርሣናት እና ቅሪተ አካሎች፣ ቀደምት ሃይማኖታዊ መጻሕፍት እና ሥዕሎችን ይዟል።

ይህ ታሪካዊ ገዳም በአካባቢው ከሚገኘው ጥቅጥቅ ደን፣ ብዝኀ ሕይወት እና ድንቅ የተፈጥሮ መልከዓ-ምድር ጋር ተዳምሮ የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስብ ልዩ የቱሪስት መስህብ ነው፡፡

የሊቦ ከምከም ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዩሐንስ ጊዜው እንደገለጹት ገዳሙ በርካታ ቅርሶችን በውስጡ የያዘ እና በቋሚ ቅርስነት የተመዘገበ መኾኑን ገልጸዋል።

እስከ ዋሻው ድረስ የሚያስገባ የመንገድ መሠረተ ልማት መኖሩንም አመላክተዋል። የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች ቦታውን እንዲጎበኙትም ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here