ተፈጥሮ ጸጋዋን ሁሉ ያፈሰሰችበት ውብ ስፍራ!

0
33

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የወለቃ፣ በቶ እና ዓባይ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ወሎ ዞን ወግዲ፣ ከላላ እና ቦረና ወረዳዎች አዋሳኝ የሚገኝ ድንቅ ቦታ ነው።

ፓርኩ ከባሕር ዳር 662 ኪሎ ሜትር፤ ከዞኑ ዋና ከተማ ደሴ ደግሞ በ182 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።

19 ሺህ 517 ሄክታር መሬት ስፋትም አለው። ፓርኩ በ2009 ዓ.ም በብሔሪዊ ፓርክነት እንደተመሠረተም መረጃዎች ያሳያሉ።

የወለቃ፣ በቶ እና ዓባይ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተሾመ ታፈሰ ወለቃ፣ በቶ እና ዓባይ ብሔራዊ ፓርክ ቦታውን በሚያዋስኑ ሦስት ትልልቅ ወንዞች የተሰየመ መኾኑን ገልጸዋል።

በፓርኩ ውስጥ እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ሌሎችም ያሉ ብርቅየ እንስሳት ይገኙበታል ብለዋል።

🌴 የብዝሃ ሕይዎት ሃብቶች፦

ከ85 በላይ የዕፅዋት ዝርያዎች እንደሚገኙም አንስተዋል። ጥቁር እንጨት፣ የቆላ ዋንዛ፣ ኮመር፣ የእጣን ዛፍ፣ በደኖ፣ አባሎ እና ዋርካ ተጠቃሾች ናቸው ተብለዋል።

ከ25 በላይ የዱር እንስሳት ዝርያዎች ማለትም ጉሬዛ፣ ቀበሮ፣ አነር፣ የዳልጋ አንበሳ፣ ጅብ፣ ጃርት፣ ሚዳቋ፣ ዝንጀሮ፣ ሽክኮ፣ የዱር ዓሳማ፣ ጥንቸል እና ድኩላ ከትመውበት እንደሚገኙም ገልጸዋል።

🦜ከ92 በላይ የአዕዋፍ ዝርያዎች መኖራቸውንም አንስተዋል። ከሦስት በላይ የዓሳ ዝርያዎች፤ ከአራት በላይ ተሣቢ እና ተራማጅ ዝርያዎች ማለትም እንደ ዘንዶ፣ አዞ እና አርጃኖ እና ሌሎች ይገኛሉ ብለዋል።

ፓርኩን ማራኪ የተፈጥሮ ሃብቶች፤ ወንዞች፣ ተራራዎቹ እና ሽንተረሮቹ ልዩ መልክን የሚያላብሱ እንደኾነም ገልጸዋል።

የፓርኩን ሃብት የመጠበቅ እና የመንከባከብ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ኀላፊው አንስተዋል። በፓርኩ ውስጥ የሚፈጸሙ ሕገ ወጥ ተግባራትን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት።

ፓርኩን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በመሥራት ሃብቱን ለማሳደግ በትኩረት እየተከናወነ ነውም ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here