“የጥበብ መገለጫ የኾነችው የአገው ጥላ (አዊት ድጋጋ)”

0
48
☂️
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕል ይወረሳል፤ ጥበብ ይፈልቃል፤ በተግባርም ይታያል፤ ትውልድም ያስቀጥላል።
በዛሬው ቅኝታችን አስገራሚ እና ድንቅ ጥበብ የሚታይበትን ባሕላዊ የአገው ጥላ ልናስቃኛችሁ ወድደናል።
የአገው ጥላ በአዊ አጠራር “አዊት ድጋጋ” በአገው ሕዝብ ባሕል፣ ታሪክ እና ማኅበራዊ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያለው ነው።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአገው ጥናት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ብርሃኑ አሳዬ የአገው ጥላ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የነገሥታት እና የመኳንንት ባለቤቶች ፈረስ ላይ ኾነው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ይጠቀሙበት የነበረ ረጅም ታሪክ ያለው ቅርስ ነው ብለዋል። ሴቶች ብቻ የሚጠቀሙት የባሕል እሴት እንደኾነም ነው የገለጹት።
የአገው ጥላ በአገው ሕዝቦች ዘንድ፦
☂️የጥበብ እና የክብር መገለጫ ነው።
☂️ከፀሐይ እና ከዝናብ ለመከላከል ይጠቀሙበት የነበርም ነው።
🏖በሰርግ ጊዜ ሙሽራ ከሰው ዐይን ለመከለል ይጠቀሙበት እንደነበርም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ታዲያ ይህ ድንቅ የባሕል ማንነት መገለጫ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ቅርስ መኾኑን ነው የገለጹት።
ከአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር አንድ ሰው ብቻ ነበር ዣንጥላዋን የመሥራት ጥበብ የነበራቸው ይላሉ ዳይሬክተሩ። እኒህ ሰው ታዲያ ጥበቡን ለዛሬው ትውልድ አውረሰዋል ብለዋል።
ለነገው ትውልድ እንዲቀጥልም መሠረት ጥለዋል ነው ያሉት። የጥበቡ ባለቤት ለ12 ሰዎች ሥልጠና እንዲሰጡ መደረጉን እና የልምድ ልውውጥ ስለመደረጉም አንስተዋል።
በዚህም የባሕል እሴቱን ከማስቀጠል ባለፈ የኢኮሮሚ ምንጭ በማድረግ ኑሮአቸውን እየመሩበት ይገኛሉ ብለዋል። ጥበባቸውን በማሳደግ በተለያዬ መጠን አሳምረው እና አስውበው እየሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል።
ነገር ግን ለዣንጥላ መሥሪያ የሚያገለግሉ ዛፎች በመጥፋት ላይ በመኾናቸው በሚበቅሉበት አካባቢ እንዳይጠፉ ጥበቃ እንዲደረግ በቅንጅት እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ዩኒቨርሲቲውም የዛፎችን ፍሬ በማፍላት ለማስፋት እየሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት። በቀጣይም በትኩረት እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።
በዞኑ በጓንጓ ወረዳ የአምቢቂ ከተማ ነዋሪ መርጌታ ሉዑል ኃይሌ የአገው ጥላን ድሮ በአባቶቻችን እና በእናቶቻችን የነበረውን ባሕል ለትውልድ ለማስቀጠል እየሠሩ መኾናቸውን ነግረውናል።
ከሰኔል፣ ከግራምጣ እና ከቀርቀሀ ዛፍ እንደሚሠራም ነው ያነሱት። ከአባቶች የቀሰሙትን ልምድ እና በተሠጣቸው ሥልጠና ያላቸውን ክህሎት በማሳደግ እየሠሩ መኾናቸውን ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ ለልጃቸው ጭምር ልምዳቸውን በማውረስ እንዲሠሩ ማድረጋቸውን አጫውተውናል።
የቀደመ የባሕል መገለጫ የኾነውን የአገው ጥላን ማስፋት እንደሚገባም ነው ሃሳባቸውን የሰጡት።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here