በኢትዮጵያ ከሚገኙ ፓርኮች መካካል አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው። ፓርኩ በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ግርማ ሞገስን ደርቦ ይገኛል።
እጅግ ውብ እና ስነ-ምሕዳራዊ ፋይዳው የላቀ የተፈጥሮ ሃብት ነው። ይህ ፓርክ በብዝሃ ሕይወት የበለጸገ ከመኾኑ ባሻገር ለአሕጉሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ ታላቅ ስትራቴጂ የኾነው አረንጓዴ ግድግዳ” Green Belt ” ዋነኛ አካል ልዩ ስፍራ እንደኾነም መረጃዎች ያሳያሉ።
የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ሙላው ሽፈራው ፓርኩ በርካታ ብዝሃ ሕይወትን በውስጡ
አቅፎ የያዘ የተፈጥሮ ሃብት ማዕከል ነው ብለዋል። 266 ሺህ 570 ሄክታር መሬት ስፋት እንዳለውም ገልጸውልናል። ፓርኩ ቀደም ባሉት ጊዚያት ጀምሮ ጥብቅ ስፍራ እንደነበረ የተናገሩት ኀላፊው ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ ሕጋዊ ጥበቃ ተደርጎለታል ነው ያሉት።
ፓርኩ በሀገር በቀል ዛፎች በተፈጥሮ አምሮ እና ተውቦ የተቀመጠ ድንቅ የሀገር ጸጋ ነው።
ለበርካታ የዱር እንስሳት እና እጽዋት ተስማሚ መኖሪያ በመኾኑ ከፍተኛ የብዝሃ ሕይወት ክምችትም አለው ብለዋል።
🐘🦌 በፓርኩ ከ32 በላይ የአጥቢ እንስሳት ከትመውበት ይገኛሉ። እንደ አንበሳ፣ ነብር፣ ዝኾን፣ ጎሽ፣ የቆላ አጋዘን፣ ድኩላ እና ሌሎችም እንስሳት ይገኙበታል። በተለይም በአፍሪካ ብቸኛው ባለ ጥቁር ጋማ አንበሳም እንደሚገኝ ገልጸዋል።
🦅🦜 ከ180 በላይ የተለያዩ የአዕዋፋት ዝርያዎች መኖሪያ ኾኖ እያገለገለገም ይገኛል።
🌿 ከ120 በላይ የእጽዋት ዝርያዎች የሚገኙበት ሲኾን እንደ ዘቢ፣ ላሎ፣ ኩመር፣ የቆላ ሽመል ፣ ወንበላ እና ሌሎችም በርከት ያሉ እጅግ ውድ የኾኑ የዛፍ ዝርያዎች ይገኛሉ። ዛፎቹ ለምርሞር የሚያገለግሉ ናቸው ብለዋል።
የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ ከተፈጥሮ ጥበቃ ባለፈ ጥልቅ ታሪካዊ ትርጉም ያለው ጭምር ነው። በፓርኩ ውስጥ በሚገኘው ኦሜላ በተባለ ቦታ “ቢዛ” የሚባል ግዙፍ ዛፍ ይገኛል። ይህ ዛፍ በታሪክ ሂደት ውስጥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደ ቤተ-መንግሥት የተጠቀሙበት እና ንጉሱ በዛፉ ላይ የራሳቸውን ጽሑፍ እንዳሰፈሩበትም ይነገራል። ይህ ቦታ ከንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ጀምሮ እንደተጠበቀ ታሪክ ያስረዳል ነው ያሉት።
ፓርኩ ለሀገሪቱ ሥነ-ምህዳር መረጋጋት የላቀ ድርሻ ያለው ነው ብለዋል። በተለይም የሰሃራ በረሃ ወደ ሀገራችን እንዳይስፋፋ የሚያግድ ከፍተኛ የመከላከል አቅም ያለው በመኾኑ አረንጓዴው ዘብ (Green belt) ተብሎ ይጠራል ነው ያሉት።
ፓርኩ ከፍተኛ የካርበን ክምችት ያለው ሲኾን ከሀገራችን የካርበን ንግድ የተሻለ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት በጥናት መመላከቱንም አንስተዋል።
የአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የተፈጥሮ ሃብትን፣ የዱር እንስሳትን፣ አዕዋፍን እና የኢትዮጵያን ታሪክ አጣቅሶ የያዘ እጅግ ጠቃሚ የቅርስ ማዕከል መኾኑን ነው የተናገሩት።
ወቅታዊ ችግሩ ፈታኝ ቢኾንም ፓርኩን የመጠበቅ፣ የመንከባከብ እና የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ይገኛል ነው ያሉት። ሕገ ወጥነትን የመከላከል ሥራ እየተሠራ ይገኛል ያሉት ኀላፊው ፓርኩን የምርምር ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት።
በተለይም ለፓርኩ የመሠረተ ልማት በማሟላት የበለጠ ማልማት እና ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ተመላክቷል።
አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ የኢትዮጵያ የኩራት ምንጭ ብቻ ሳይኾን፣ የአፍሪካን መሬት ከድርቅ እና ከበረሃማነት የመታደጊያ ጋሻም ነው። የዚህን ፓርክ ደን እና የዱር እንስሳት መጠበቅ፣ ለወደፊት ትውልድ አረንጓዴ እና አስተማማኝ ምድርን ለማውረስ በቁርጠኝነት መሥራት የሁሉም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል።
#AlatashNationalPark #VisitEthiopia #AfricanWildlife #GreenBelt #Biodiversity
ዘጋቢ፦ሥራውድንቅ ደሳለው









