“የምኒልክ መስኮት” እንዴት ስያሜውን አገኘ?

0
30
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሶና ወረና ወረዳ የሚገኘው እና “ገማሳ ገደል” በመባል የሚታወቀው “የምኒልክ መሥኮት” ከፍተኛ የቱሪዝም እምቅ ሃብት ያለው በመኾኑ ይበልጥ ሊለማ እና ሊተዋወቅ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች እና የአካባቢው አስጎብኝዎች ይገልጻሉ።
ከአዲስ አበባ በሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 174 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከአስፋልት መንገድ ዳር የሚገኘው ይህ ስፍራ ከባሕር ወለል በላይ 3 ሺህ 500 ሜትር ከፍታ ያለው ድንቅ የተፈጥሮ መስህብ ነው።
ቦታው በእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እና ከስምጥ ሸለቆ መፈጠር ጋር ተያይዞ በሁለት ግዙፍ ተራሮች መካከል የተገመሰ በመኾኑ በአካባቢው ማኅበረሰብ “ገማሳ ገደል” ተብሎ ይጠራል።
ዳግማዊ አጼ ምኒልክ የቤተ መንግሥት መቀመጫቸውን ከአንኮበር ወደ ሰላ ድንጋይ በሚያዛውሩበት ወቅት የተራራውን ክፍተት እንደ መስኮት በመጠቀም የወፍ ዋሻ ጥብቅ ደንን፣ የአፋር እና አዋሽ አካባቢዎችን እንዲሁም የጠላት እንቅስቃሴን ይቃኙበት ስለነበር “የምኒልክ መሥኮት” የሚል ስያሜ እንደተሰጠው ይነገራል።
ዓመቱን ሙሉ በለምለም እፅዋት እና በጉም የተሸፈነው ይህ ደጋማ ስፍራ ብርቅዬዋን “አንኮበር ሰሪን” የተባለች ወፍ፣ የጭላዳ ዝንጀሮዎችን እና ሀገር በቀል እፅዋትን በውስጡ ይዟል።
በተጨማሪም የአካባቢው ወጣቶች በማኅበር ተደራጅተው ባሕላዊ ኮፍያዎችን እና የዕደ-ጥበብ ውጤቶችን በማምረት ለጎብኝዎች በማቅረብ ላይ ይገኛሉ።
በሰሜን ሸዋ ዞን የባሶና ወረና ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቱሪስት መዳረሻ ልማት ባለሙያው አጸደ ተስፋ ስፍራው ለጎብኝዎች ምቹ እና በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል በመኾኑ የተፈጥሮ እና ታሪክ ውህደት የኾነውን ይህን መዳረሻ ይበልጥ በማልማት እና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here