የተፈጥሮ ድንቅ ሥራ፤ የውኃዎች የመከባበር ጉዞ ትዕይንት

0
79
🇪🇹“ዓባይ በጣና ላይ እንዴት ቀለደበት፣
ለአንድ ቀን ነው ብሎ ለሺህ ዓመት ሄደበት” ተብሎ ተገጥሟል። የጉዞውን ትዕይንት ያየ ሰው ግን ጉዳዩ የመቀለድ ሳይኾን የመከባር እና በክብር የመሸኛኘት ትዕይንት ነው።
በባሕር ዳር ከተማ እና ዙሪያዋ በርካታ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን የሚገኙ ቢኾኑም እጅግ አስገራሚው እና “እንዴት ሊኾን ቻለ?” የሚል ጥያቄን የሚያስነሳው ትዕይንተ ተፈጥሮ ግን የዓባይ እና የጣና የሸኝ እና ተሽኝ አይነት ጉዞ ነው።
ጣና ሞገዱን አረጋግቶ በጥልቅ እርጋታ ውስጥ በመኾን ዓባይ በመሐሉ ላይ ሰንጥቆት እንዲያልፍ መንገድ ይከፍትለታል።
በጣና ሐይቅ ላይ ደብረ ማርያም ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተገኘ ሰው የባለግርማው ሐይቅ እና የሩቅ ተጓዡ ወንዝ መሸኛኛ ቦታ ያገኛል። የዓባይ ውኃ ከጣና ውኃ የተለየ ቀለም ይዞ ለብቻ ተጥመልምሎ ወጥቶ ሲሄድም በዓይኑ እየተመለከተ ትዕይንተ ተፈጥሮን ያደንቃል።
ውኃ በውኃ ላይ ሲጓዝ እንዴት ይታያል? ይህንን ለማብራራት ቃላት አቅም አይኖራቸውም፤ በአካል ላየው ሰው ግን ግርምትን ፈጥሮ መንፈስንም ያድሳል።
ባሕር ዳር በቀስተደመና ቀለም ትናኝ የታጀበው ጭስ ፏፏቴ፣ በሐይቅ ላይ ገዳማት እና በሕዝቦቿ ድንቅ ባሕል እና እሴት የጎብኝዎችን ልብ በጥልቀት የምትማርክ ልዩ ከተማ ናት።
በተለይም ከግሽ ተራራ ግርጌ ፈልቆ፣ ወደጣና ጉያ የገባው ዓባይ ጡንቻውን አፈርጥሞ ጉዞውን የሚጀምርባት ከተማም መኾኗ ስመ ጥሩ ያደርጋታል። ተፈጥሮ እና ታሪክ በጥበብ የተዋሐዱባት ምድርም ናት።
ጣና ሐይቅ ለከተማዋ ተፈጥሯዊ ውበት ብቻ ሳይኾን ዋና መለያ ምልክቷም ነው። በሐይቁ ሰፊ የውኃ አካል ላይ በተበተኑ ደሴቶች ውስጥ ለዘመናት የጸኑ ጥንታዊ ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ። ጎብኝዎች በጀልባ ተጉዘው እነዚህን ታሪካዊ ስፍራዎች ሲጎበኙ፣ ከዘመናት በፊት የነበሩ ድንቅ የጥበብ፣ የታሪክ እና የባሕል ቅምሻዎችን በጥልቀት ያጣጥማሉ።
ባሕር ዳርን ከሌሎች ከተሞች ለየት የሚያደርጋት ሌላው አስደናቂ ገጽታ ደግሞ በመንገዶቿ ዳርቻ ጃንጥላ ይዘው ተሰልፈው እንግዶችን “እንኳን ደህና መጣችሁ” የሚሉ የሚመስሉት እና ከተማዋን ያሸበረቋት ባለጎፈሬ ዘንባባዎቿ ናቸው።
እነዚህ ማራኪ ዘንባባዎች ለከተማዋ ሞቃታማ የጸሐይ ብርሃን ቀዝቃዛ ጥላ ከመስጠታቸው ባሻገር፣ ለአካባቢው አረንጓዴ እና ማራኪ ገጽታን ያላብሳል። ከተማዋን ከተፈጥሮ ውበቷ እና ከታሪካዊ ቅርሶቿ ባሻገር፣ የነዋሪዎች ደግነት እና እንግዳ ተቀባይነት ለጎብኝዎች ልዩ ምቾት እና ደኅንነትን ያላብሳል።
ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቾትን ለጎብኝዎቿ ደግሞ የማይረሳ ውብ ትዝታን የምትለግስ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘውድ ናት።
✍️በሀኒፍ ሀምዛ (ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሚኮ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here