ባሕር ዳር: ሚያዝያ 07/2018 ዓ.ም (አሚኮ) መምህር እሱባለው ክንዴ የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በእንጅባራ እና አካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ልዩ ቦታ ከሚሰጣቸው የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች መካከል ዘንገና ሐይቅ አንዱ መኾኑን ነግረውናል። ሐይቁ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚከወንበትም ገልጸዋል።
የአካባቢውን ባሕል እና እሴቶች ለማስተዋወቅ አጋዥ እንደኾነም ነው የተናገሩት። የሐይቁ አካባቢ ቢለማ ለአካባቢው ማኅበረሰብ እና ለመንግሥት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢኾንም እስካሁን አልለማም ነው ያሉት።
ለሐይቁ ሰው የጨመረለት ነገር አለመኖሩንም ተናግረዋል። ሐይቁ ተፈጥሮ በሰጠው ነገር ብቻ ይጎበኛል፣ ስሙም ጎልቶ ይጠቀሳል ብለዋል።
በሐይቁ አካባቢ መገንባት ጀምረው የነበሩ ሁለት ሎጅዎች እንደነበሩም አንስተዋል። የእነዚህ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሂደት ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ እንደቆየ እና አሁን ላይም ወደ ሥራ እንዳልተገባ ጠቁመዋል።
የተቋረጠበት ምክንያትም ዕውቅና እንደሌላቸው ነው ያጫወቱን። በሐይቁ ዙሪያ የሚሠሩ ተግባራት መጓተትም እንዲቀረፍ ጠይቀዋል።
ይህ ችግር ከተቀረፈ አማራ ክልል ውስጥ አሉ ከሚባሉ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዱ ይኾናል ብለዋል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ቃለአብ ከኀሊ ዘንገና ሐይቅ በክልሉ እና በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትልቅ የቱሪስት መስህብ ይኾናሉ ተብለው ከተለዩት ቦታዎች አንዱ መኾኑን ነግረውናል።
ሐይቁ አካባቢ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ባለመጠናቀቃቸው እና የሐይቁ አካባቢ ባለመልማቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ እና መንግሥት ሊያገኙት የሚገባ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል።
አሁን ላይ የሐይቁ አካባቢ የሀገራዊ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ፕሮጀክት አካል እንዲኾን ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነም ኀላፊው አንስተዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
# ዘንገና# ቱሪዝም# አማራ# ኢትዮጵያ#
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









