አጼ ይሙቱ “አንጎትኛ” የወልቃይት የሠርግ ሥነ ሥርዓት።

0
53
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንድ አካል እና አንድ አምሳል ለመኾን ጥንዶች በመፈላለግ እና በቤተሰብ አማካኝነት አጋርን በማሳጨት ጋብቻን ይፈጽማሉ።
በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ማኅበረሰቡ እንደ ባሕላዊ ሥርዓታቸው በድምቀት የሠርግ ሥርዓትን ይከውናሉ።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ደግሞ ይህ የሠርግ ሥነ ሥርዓት “አንጎትኛ” በሚል ስያሜ ይጠራል።
የወልቃይት ነዋሪ እና “የአንጎትኛ” የሠርግ ሥነ ሥርዓት መጽሐፍ ደረሲ ልማት ሙሉ የወልቃይት የሠርግ ሥርዓት ከጎንደር ማኅበረሰብ ባሕል ጋር ልዩ ትሥሥር እንዳለው አንስተዋል።
✍️ የሽምግልና ሥርዓት
🤵 የወንድ ቤተሰብ ወደ ሴት ቤተሰቦች በመሄድ ልጅህን ለልጀ በማለት የሽምግልና እና የቃል ኪዳን ሥርዓትን ይፈጽማሉ ብለዋል።
👰 በሴቷ ቤተሰብ ውላችን ምንድን ነው ተብለው ሲጠየቁ “አንጎትኛ” በማለት የወንድ ቤተሰብ ይመልሳሉ ነው ያሉት።
ቤተሰቡን ያስተዋወቀው ሸማግሌ “አዋቂ” ተብሎ እንደሚጠራ ያነሱት ደረሲ ልማት ሙሉ በመካከላቸው ኾኖ የሽምግልና የቃል ኪዳን ሥርዓቱ እንደሚፈጸምም ገልጸዋል።
💍 ቃል ኪዳናቸውንም አጼ ይሙቱ ወይም መንግሥት ይሙት በማለት በመሐላ ይስማማሉ ነው ያሉት። በአጼዎቹ ስም መማላቸው ቃላቸው እንደማይታጠፍ ለማሳወቅ እንደኾነም ደራሲው ገልጸዋል።
የሴት ቤተሰቦች ጥንድ በሬ እና የቁም እንስሳ ጨምረው እንደሚሠጡም ገልጸዋል። በሠርግ ቀን ወርቅ፣ አልባሳት እና የተለያዩ ጌጦች የወንድ ቤተሰብ እንደሚሰጥም ነው የተናገሩት። ኩታ፣ ጋቢ እና ጣቃ ልብስ ለወንድ ሙሽራ በሽልማት ይበረከታል ነው ያሉት።
የሠርግ ባሕል ሥርዓቱ ከአጼ ፋሲለደስ ዘመን ጀምሮ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሎጋው ሽቦ እየተባለ በጎንደርኛ ባሕል እንደሚዘፈንም አንስተውልናል።
“አንጎትኛ” ቃሉ ብዙ ትርጉም እንዳለው አንስተው በዋናነት “ለቃል መታመን” መኾኑን ተናግረዋል። ቤተ ዘመድ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ የደጋሽን ቤተሰብ በጉልበት፣ በገንዘብ እና በዓይነት ይደግፋል ብለዋል።
✍️ በሠርጉ ላይ የሚሰሙ ግጥሞች
👉 ለአካባቢው
እስኪ በስመ አብ ብየ ልጀምር ሰላምታ፤ ለተቀመጥንበት ላለንበት ቦታ፤ ወልቃይት ጠገዴ ጎንደር በጌ ምድር የሀገር መከታ፤ ተብሎ ይገጠማል።
👉 ለሙሽሪት እናት
የሙሽሪት እናት ውጭ ተጠየቂ፤
የጠመቅሽው ጠላ ወይን ነው አረቂ፤
የሙሽሪት እናት በጠመቀች ጊዜ፤ አስመስላ ቢራ፣ ወጥ በሠራች ጊዜ ሽታው የሚበላ፣ በፈተለች ጊዜ ሰንጥቃ እንደ ጭራ፣ መልከ መልካም ሴት ናት ሀገር የምታኮራ፤ ተብላ በሠርጉ ትወደሳለች።
👉 ለሙሽሪት አባት ደግሞ
የሙሽሪት አባት ደስ ይበልህ ደስ፤
ፈረስ ያስጋልባል የሠራኸው ዳስ እየተባለ ይወደሳል።
👉 የሙሽራው ሚዜዎች በልተው ጠጥተው ሲወጡ
በሉ እንግዲህ ሸኙኝ ልሂድ ወደ ሀገሬ፤ እንዳልሰለቻችሁ እንዳይበዛ ነውሬ፤ እያሉ እንደሚወጡም ደረሲ ልማት ሙሉ ገልጸዋል።
👉 የሴት ቤተሰቦችም
እንጫወት እንጅ እየተዝናናነ፣
ቀን ፈረሰኛ ነው እንዳይደርስብነ።
በማለት እንዲቆዩ ይጠይቃሉ።
ይህ የወልቃይት ጠገዴ የሠርግ ሥርዓት ባሕል፣ ወግ እና ታሪክ የሚገለጽበት መኾኑንም ጠቅሰዋል። ታሪክን መጠበቅ ማንነትን ለማጽናት እንደሚያግዝም ተናግረዋል።
#ባሕል# ወልቃይት# አማራ# ኢትዮጵያ#
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here