ባሕር ዳር: ሚያዝያ 09/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጉና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ በደቡብ ጎንደር ዞን ከደብረ-ታቦር ከተማ በስተደቡብ ምሥራቅ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።
በሦሥት ወረዳዎች እና በ11 ቀበሌዎች የሚዋሰን ሲኾን 4 ሺህ 615 ሄክታር መሬት የቆዳ ስፋት አለው።
ጉና እና አካባቢው ውርጭ እና ውርጭ ቀመስ ሥርዓተ ምሕዳሮች ይስተናገዱበታል። በክረምት ወቅት የተራራው አናት በበረዶ ተሸፍኖ ስለሚታይ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የበረዶ መፍያው እየተባለ ይጠራል። ይህ ሥነ ምሕዳር የአካባቢውን ነዋሪዎች አኗኗር፣ ባሕል እና እሴት ወስኖ እናገኘዋለን።
ጉና የበርካታ ብዝኀ ሕይወት መገኛ ነው። እንደ ጭላዳ ዝንጀሮ እና ቀይ ቀበሮ ያሉ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ብርቅዬ እንስሳት እና አዕዋፋት መጠለያም ነው። እፅዋት ተንሰራፍተው የሚገኙበት ድንቅ ሥፍራም ነው ጉና።
ጉና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ የውኃ ማማ ነው። የተከዜ፣ የዓባይ እና የጣና ተፋሰስ መነሻ፤ 41 ወንዞች እና 77 ምንጮች ከጉና ተነስተው ወደ ተከዜ፣ ዓባይ እና ጣና ተፋሰስ እንደሚፈሱ የጥብቅ ሥፍራው ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሙሉ አበጀ ተናግረዋል።
በአዋሳኝ ቀበሌዎች ጠባቂዎች ተመድበው እና ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ጥብቅ ሥፍራውን ከጥፋት ለመጠበቅ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
አቶ ሙሉ ጥብቅ ሥፍራው ላይ የሚሠሩ ዩኒቨርሲቲዎች እና የልማት ድርጅቶች እንደነበሩም አስታውሰዋል። አሁን ላይ በጸጥታ ችግሩ ምክንያት ሥራቸውን በማቆማቸው በሚፈለገው ልክ ለማልማት እና ለመጠበቅ አስቸጋሪ አድርጎታል ነው ያሉት።
በአማራ ክልል የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ልማት እና ጥበቃ ዳይሬክተሩ አበባው ዓባይነህ (ዶ.ር) ጉና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ የተከዜ፣ የዓባይ እና ጣና ተፋሰስ መነሻ የኾነ ከአማራ ክልል አልፎ የኢትዮጵያ እና የሕዝቦቿ የሕልውና መሠረትም መኾኑን ገልጸዋል።
በጥብቅነት የተከለለውም ሥነ ምሕዳሩን በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ እና ማኅበረሰቡን ከሃብቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው ብለዋል።
ነገር ግን በሰላም እጦቱ ምክንያት በክልሉ በችግር ውስጥ ከሚገኙ ጥብቅ ሥፍራዎች መካከል ኾኗል ነው ያሉት። ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር የሕገ ወጥ እርሻ መስፋፋትን፣ ሕገ ወጥ የቤት ግንባታን፣ የእንስሳት አደን እና ግድያን ለመከላከል እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት በሰላም እጦቱ የተነሳ የልማት ድርጅቶች እና ተቋማት ሥፍራውን የማልማት እና የመጠበቅ ሥራ እንዳይሠሩ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ይህን የውኃ ማማ ካለበት ችግር ለማላቀቅ በቀዳሚነት ሰላም ያስፈልጋል ነው ያሉት። የክልሉን መንግሥት እና የአጋር አካላትን ልዩ ትኩረትም እንደሚፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሰላም እጦቱ ከጉና የማኅበረሰብ ጥብቅ ሥፍራ በተጨማሪ ሌሎች ጥብቅ ሥፍራዎችን እና ፓርኮችንም ጎድቷል ብለዋል።
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









