የተዋበው ጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ

0
69
ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ይገኛል።
ፓርኩ አረንጓዴ ካባ የለበሰ ውብ ምድር ነው። ተፈጥሮ ጸጋ ያበዛለት አስደናቂ ሥፍራ ነው። ይህ ግርምትን የሚጭረው፣ መንፈስን የሚያድሰው አረንጓዴ ምድር የበርካታ እንስሳት ቤት ነው።
የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የሥነ ምሕዳር ክትትል እና ቁጥጥር ቡድን መሪ መሠረት ብርሃኑ ፓርኩ ከባሕር ዳር 417 ኪሎ ሜትር፣ ከምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ገንዳ ውኃ 133 ኪሎ ሜትር እና ከወረዳው ዋና ከተማ አብርሃጅራ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፓርኩ 18 ሺህ 691 ሔክታር ይሸፍናል ተብሎ ይገመታል ነው ያሉት። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በብሔራዊ ፓርክነት መመዝገቡንም ገልጸዋል። አረንጓዴው ቀበቶ እየተባለም ይጠራል ነው ያሉት።
✍️ በፓርኩ ውስጥ ከ27 በላይ እንስሳት ይገኛሉ። የቆላ አጋዘን፣ ነብር፣ ቀበሮ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ጅብ፣ ዝንጀሮ፣ ቀይ ጦጣ፣ አነር እና ሌሎች የዱር እንስሳት እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
✍️ ከ57 በላይ የተለያዩ የአዕዋፍ ዝርያዎች መኖራቸውንም ተናግረዋል። እንደ ነጭ ጀርባ፣ የአፍሪካ ጥንብ አንሳ፣ጉራማይሌ፣ ግንደ ቆርቁር እና ሌሎችም ይገኛሉ። በአይነታቸው የተለዩ እንዳሉም ቡድን መሪው ጠቁመዋል።
✍️ ከ81 በላይ የእፅዋት ዝርያ የነበረው ፓርኩ አሁን ላይ ደግሞ ከ130 በላይ እንደ ዋሊያ፣ መቀራ፣ ሰርኪን ፣ የእጣን ዛፍ፣ የዞቢ እና የቆላ ቀርቀሃ ወይም ሸመልን ጨምሮ የእፅዋት አይነቶች መገኛም እንደኾነ ጠቁመዋል።
የፓርኩን የብዝኀ ሕይወት ድኅንነት የመጠበቅ እና የማልማት ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም አንስተዋል።
የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው በመጠበቅ እንደ ሰደደ እሳት አይነት አደጋዎችን የመከላከል ሥራ መተግበራቸውን ነው የተናገሩት።
ፓርኩ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ሀብት ከማነቃቃት ባለፈ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመከላላል ትልቅ አቅም እንዳለውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here