በልበሊት- የበረሃው ለምለም 🌿

0
52

 

ባሕር ዳር: ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራፈ ቅዱሳን በልበሊት ኢየሱስ አንድነት ገዳም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በእንሳሮ ወረዳ ይገኛል። ገዳሙ ተፈጥሯዊ እና መንፈሳዊ ታሪክን በአንድነት አቀናጅቶ የያዘ ድንቅ ስፍራ ነው።

ታሪካዊ ቦታው:-
🚙 ከአዲስ አበባ ወደ መርሀቤቴ በሚወስደው መንገድ በ152 ኪሎ ሜትር ላይ፣ ከደብረ ብርሃን በ105 ኪሎ ሜትር እና ከወረዳው መቀመጫ ለሚ ከተማ ደግሞ በ22 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሰማይ ጠቀስ በኾኑ እና በሰንሰለታማ ተራራዎች በተከበበው አስደናቂ መልክዓ ምድር ውስጥ ይገኛል።

ገዳሙ:-
👉 ጥንታዊ ዋሻዎችን፤ ከከርሰ ምድር የሚፈልቁ የተፈጥሮ ምንጮችን፤ ለምለም ዕፅዋቶችን በውስጡ ይዟል።

በኢትዮጵያ ካሉ ጥንታዊ ገዳማት መካከል ከዋልድባ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ የጥበብ ቤት እንደኾነም ይነገራል።

የገዳሙ ሃይማኖታዊ መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ በስደት ዘመኑ ከእናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር ካረፈባቸው አምስት ገዳማት መካከል አንዱ እንደኾነ ይታመናል። በዚህም ወቅት ጌታ ለእናቱ ድንግል ማርያም ስፍራው እስከ ዕለተ ምጽዓት ድረስ ከርሃብ እና ከቸነፈር የተጠበቀ እንዲኾን ቃል ኪዳን እንደሰጣት በታሪክ መሰነዱም ይገለጻል።

👉 የገዳሙ መገለጫዎች፦
የእንሳሮ ወረዳ ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ማንደፍሮ ተካልኝ ገዳሙ በውስጡ አምስት አብያተ ክርስቲያናትን አቅፎ የያዘ ነው ብለዋል።

ከተለያዩ ህመሞች የሚፈውስ ጸበል እና በአቡነ ተክለሃይማኖት ዘንግ ፈልቆ ለመዋኛነት የሚያገለግል ገንዳ፤ አቡነ ዜናማርቆስ እና አቡነ ተክለኃይማኖት የጸለዩበት እንድሁም እስከ እየሩሳሌም የሚያስኬድ ምስጢራዊ ዋሻ እንዳለውም በአፈ ታሪክ እንደሚነገር አንስተዋል።

👉 በልበሊት ስያሜውን እንዴት አገኘ?

ከዘመናት በፊት ዓይነ ስውር የነበረች እና በልበሊት የተባለች ሴት ወደ ቦታው መጥታ እንደነበር ይነገራል ነው ያሉት። እንደመጣችም ዐይኗ በርቶላት በዚያው እንደመነኮሰት ታሪኩ ያስረዳል ብለዋል።

ይህችም እናት ፊቁጦር ከተባለ ልጇ ጋር በ5 ሺህ ግመሎች ንብረቷን አስጭና በማስመጣት ለገዳሙ ገቢ አድርገዋል ነው ያሉት። ከኢየሩሳሌም አፈር በማስመጣት በዕንቁ እና በእብነበረድ በማስጌጥ ሁለት ቤተክርስቲያን እንዳሳነጹ ይነገራል ብለዋል።

ገዳሙ አሁን፦
👉 በገዳሙ መነኮሳት የእጅ-ጥበብ ሥራዎችን እየሠሩ በመሸጥ ይተዳደራሉ።
👉 ገዳሙ ዘመናዊ የግብርና አሠራሮችን በመከተል በአትክልት እና ፍራፍሬ የተከበበ ለምለም ገዳም ነው።

ታሪክን ማወቅ እና መረዳት ራስን ማወቅ ነው። ስንቶቻችን ለታሪኮቻችን ትኩረት እንሰጥ ይኾን?

#አሚኮ #በልበሊት #ቱሪዝም #አማራ #ኢትዮጵያ#

በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here