የኮሪደር ልማቱ ጣና ሐይቅን ከቆሻሻ ታድጓል።

0
17

 

ባሕር ዳር: ግንቦት 04/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳርን የማስዋብ እና ተፈጥሮ ከለገሰቻት ውበቷ በተጨማሪ አምራ እንድትታይ ለማድረግ የሚደረገው ሥራ ቀጥሏል።

ባሕር ዳርን ውብ ከማድረግ ሥራው በተቃራኒ ደግሞ ለከተማዋ ውበት የማይጨነቁ እና ቆሻሻዎችን በየቦታው የሚጥሉ ሰዎችም ይታያሉ። ይህ ደግሞ ባሕርዳርን ጽዱ ለማድረግ እየተሠራ ካለው ሥራ ጋር ተቃራኒ ነው።

የባሕር ዳር ከተማ የአካባቢ ጥበቃ፣ ጽዳት እና ውበት ኀላፊ ጽጌሬዳ አበበ ባሕር ዳር የጎብኝዎች መዳረሻ እና ተመራጭ ከተማ ናት ብለዋል።

ይህችን ከተማ ውብ እና ማራኪ በማድረግ ለነዋሪዎቿም ኾነ ለጎብኝዎቿ ይበልጥ ምቹ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ባሕር ዳር ጽዱ እንድትኾን የጽዳት ማኅበራትን በማደራጀት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በዚህም ባሕር ዳር በየቀኑ እየጸዳች ነው ብለዋል።

በከተማዋ ወሳኝ በሚባሉ ቦታዎች ላይ ትንንሽ የሚመስሉ ቆሻሻዎችን መጣያ የማስቀመጥ ሥራ መሥራቱን አንስተዋል።

እያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ ከመንገድ 20 ሜትር እና እያንዳንዱ ድርጅት ደግሞ እስከ 50 ሜትር ባለው ርቀት እንዲያጸዳ እና እንዲያለማ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መኾኑን ጠቁመዋል።

የባሕር ዳርን ጽዳት በማይጠብቁት እና ፍሳሾችን መንገድ ላይ በሚጥሉት ላይ እስከ 100 ሺህ ብር ቅጣት ያስቀጣል ብለዋል። አሁን ላይ ከተማ አሥተዳደሩ ስለጉዳዩ ጥቅሙን በማስረዳት ሁሉም የከተማዋን ጽዳት እንዲጠብቅ የማድረግ ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት ጣና ችግር ላይ ነው፤ ትልልቅ ሆቴሎች ሳይቀሩ ፍሳሻቸውን ወደ ጣና ይለቃሉ የሚባለው እውነታ የተገለጠው በኮሪደር ልማቱ ነው ብለዋል። በርካታ ተቋማት ፍሳሻቸውን ወደ ጣና እየለቀቁ ጣናን አደጋ ላይ ጥለው መቆየታቸው በተጨባጭ የኮሪደር ልማቱ አጋልጧል ነው ያሉት።

አሁን ላይ ጣና ከነበረበት አደጋ መውጣቱን ተናግረዋል። አሁንም ግን ጨለማን ተገን በማድረግ በምስጢር ከኮሪደር ልማት ማፋሰሻ ቦታዎች ጋር ፍሳሻቸውን ለማገናኘት የሚጥሩ እንዳሉ እና በክትትል የተያዙ እንዳሉም አስረድተዋል።

ማኅበረሰቡ እነዚህን ሕገ ወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎችን መከላከል እና ሥራቸውን በማጋለጥ ለከተማዋ ጽዳት እና ልማት የበኩሉን እንዲወጣም አሳስበዋል።

ዘጋቢ:- ምሥጋናው ብርሃኔ

#ኮሪደርልማት #ባሕርዳር #ኢትዮጵያ

የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ

https://linktr.ee/Amharamediacorporations

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here