ባሕር ዳር: ሚያዝያ 12/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ በአማራ ክልል በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ይገኛል።
ፓርኩ አረንጓዴ ካባ የለበሰ ውብ ምድር ነው። ተፈጥሮ ጸጋ ያበዛለት አስደናቂ ሥፍራ ነው። ይህ ግርምትን የሚጭረው፣ መንፈስን የሚያድሰው አረንጓዴ ምድር የበርካታ እንስሳት ቤት ነው።
የጎደቤ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት የሥነ ምሕዳር ክትትል እና ቁጥጥር ቡድን መሪ መሠረት ብርሃኑ ፓርኩ ከባሕር ዳር 417 ኪሎ ሜትር፣ ከምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና ከተማ ገንዳ ውኃ 133 ኪሎ ሜትር እና ከወረዳው ዋና ከተማ አብርሃጅራ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል ብለዋል።
ፓርኩ 18 ሺህ 691 ሔክታር ይሸፍናል ተብሎ ይገመታል ነው ያሉት። ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በብሔራዊ ፓርክነት መመዝገቡንም ገልጸዋል። አረንጓዴው ቀበቶ እየተባለም ይጠራል ነው ያሉት።
የፓርኩን የብዝኀ ሕይወት ድኅንነት የመጠበቅ እና የማልማት ሥራ ሲከናወን መቆየቱንም አንስተዋል።
የአካባቢው ወጣቶች ተደራጅተው በመጠበቅ እንደ ሰደደ እሳት አይነት አደጋዎችን የመከላከል ሥራ መተግበራቸውን ነው የተናገሩት።
ፓርኩ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ሀብት ከማነቃቃት ባለፈ የአየር ንብረት ተፅዕኖን ለመከላላል ትልቅ አቅም እንዳለውም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !









