ሁለገቡ ተክል – ቅርቀሃ

0
5
ባሕር ዳር፡ ግንቦት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቅርቀሃ ከ5 ሺህ ዓመት በፊት በቻይና እንደተገኘ መረጃዎች ያሳያሉ።
በደጋማ አካባቢዎች የሚበቅል ሲኾን በአፍሪካ፣ በአሜሪካ እና እስያ አሕጉሮች ላይ በስፋት እንደሚበቅል በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችም ያመላክታሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃም ከ1 ሺህ 400 በላይ የቅርቀሃ ዝርያዎች ይገኛሉ።
በዓለም ላይ ቶሎ ከሚያድጉ ተክሎች አንዱ እና ዋነኛው ቀርቀሃ እንደኾነም ይገለጻል። በየቀኑ 60 ሴንቲ ሜትር እንደሚያድግም በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።
👉 ቅርቀሃ በኢትዮጵያ 🇪🇹
በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን ሄክታር የሚኾን መሬት በቅርቀሃ ተክል የተሸፈነ እንደኾነ ይገለጻል። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በቅርቀሃ ምርት ቀዳሚ ሀገር እንድትኾን አድርጓታል። 23 ዓይነት የቅርቀሃ ዝርያዎችምችም ይገኛሉ። አስገራሚው ነገር ቅርቀሃ ከምግብነት እስከ ፋብሪካዎች ግብዓትነት የሚውል ሁለገብ ተክልም ነው።
👉 ቅርቀሃ ለምግብነት !
ቻይና እና ሕንድ ቅርቀሃን ለምግብነት ከሚያውሉ የዓለማችን ሀገሮች ቀዳሚዎቹ ናቸው። ቡቃያውን በመቀቀል ለምግብነት ይጠቀሙበታል። የተቀቀለውን ከቃሪያ እና ከሌላ ምግብ ጋር ቀላቅለው ይመገቡታል።
በኢትዮጵያ ጥሬ ስጋ ቆርጦ የሚሰጥ ሰው እንደሚወደደው ሁሉ ቡቃያውን ቅርቀሃ እንደ ሥጋ ቆርጦ የሚሰጥ ሰው በቻይናውያን ዘንድ ይወደዳል።
👉 ቅርቀሃ ለጤና!
እንደ ጥናቱ ከኾነ ቅርቀሃ ለሰው ልጆች ጤና በርካታ ጥቅሞችን ይሰጣል ቢባል ሊያስገርም ይችላል። ቅርቀሃ በርካታ ቫይታሚን እና ሚኒራሎችን በውስጡ የያዘ ነው። የቀርቀሃ ምርት ኮሊስትሮልን ከሰውነት ይቀንሳል። ከቅርቀሃ የሚገኘው ፋይቨር ንጥረ ነገር ኮሊስትሮልን በመቀነስ በልብ ህመም የመያዝን ዕድልን በጣም ይቀንሳል።
በቅርቀሃ ውስጥ የሚገኘው ዝቅተኛ ካርቦሀይድሬት መጠን ስኳር እና ደም ግፊት በመሰሉ በሽታዎች እንዳንያዝ ያገለግላል። ለጤና ጠቃሚ የኾኑ ፖታሺየም፣ካልሺየም፣ ዚንክ፣ ማግኒዥየም፣ ቫይታሚን እና አይረንን በውስጡ የያዘ አስገራሚ ተክልም ነው።
👉 ቅርቀሃ ለቤት እቃዎች መሥሪያ
ቅርቀሃ በዘመናዊ መንገድ ሶፋ፣ ወንበር፣ የምግብ ጠረጴዛ፣ ዘንቢል፣ ግድግዳ ላይ የሚሰቀሉ ጌጣጌጦች፣ የምኝታ አንሶላ፣ የዶሮ ቤቶችን ለመሥራት እና ለሌሎችም የሚያገለግል ተክል ነው። ከቅርቀሃ የማይሠራ የቤት እቃ የለም ማለት ይቻላል።
👉 ቅርቀሃ ለአንዱስትሪ ግብዓትነት
ቅርቀሃ ተክል ለፋብሪካዎች ወረቀት ማምረቻነት ይጠቅማል። በዚህ ሥራ ቻይና እና ሕንድ ይጠቀሳሉ። ሕንድ 3 ሚሊዮን ቶን የሚደርሰውን የቅርቀሃ ምርት ወረቀት ለመሥራት በየዓመቱ በግብዓትነት ታውላለች። በተጨማሪም የተለያዩ ኬሚካሎችን ለመሥራት ጥቅም ላይ እንደሚውል የዘርፉ ምሁራን ያትታሉ።
👉 ቅርቀሃ በአዊ
በአዊ ቅርቀሃን አርሶ አደሮች በየጓሮው እና በየማሳው የመትከል ልምዱ ከፍ ያለ ነው። ቅርቀሃን ከጎረቤት መለመን እንደ ነውር ይቆጠራል።
አካባቢው በቅርቀሃ ምርት ታዋቂ ቢኾንም ለአጥር፣ ለቤት መሥሪያ እና ወንበር አገልግሎት ከማዋል ውጭ ለሌላ ሲጠቀሙት አይስተዋልም።
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የአዊኛ ቋንቋ እና ሥነ ጹሑፍ ትምህርት ክፍል ውስጥ መምህር የኾኑት እሱባለው ክንዴ በቅርቀሃ ዙሪያ የሁለተኛ ዲግሪ መመረቂያ ጥናት አድርገዋል። ባካሄዱት ጥናትም የአዊ ሕዝብ ቅርቀሃ ላይ ያለውን ሀገር በቀል ዕውቀት በስፋት ዳስሰዋል።
የአዊ ሕዝብ ቅርቀሃን ድሮም ቢኾን አገልግል፣ እንዝርት፣ የወጥ ማማሰያ ማንኪያ፣ ዘንቢል፣ በር መዝጊያ፣ የንብ ቀፎ፣ ወንበር እና ሌሎችን እቃዎች በመሥራት ሲጠቀም መቆየቱን ተናግረዋል።
የአዊ ሕዝብ “ከቅርቀሃ እና በቆሎ ምርት የሚጣል የለም” የሚል የቆዬ አባባል መኖሩንም ገልጸዋል። ይህንን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው ተክል ታዲያ ሌሎች ሀገሮች እንደሚጠቀሙበት ሁሉ መጠቀም እንደሚገባም መክረዋል።
አርሶ አደሮች በክረምት ወራት ይተክሉታል፤ ወቅት ጠብቀውም ኅዳር እና መጋቢት ላይ ይቆርጡታል ነው ያሉት መምህሩ።
የቅርቀሃ ምርት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው ያሉት መምህር እሱባለው እንጅባራ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች የምርምር ተቋማት ተክሉ እንዳይጠፋ ዘሩን በማሻሻል ምርቱ እንዲጨምር መሥራት ይገባቸዋል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ ወቅትም የቅርቀሃ ተክል እንዲተከል ሁሉም አካል በትኩረት መሥራት እንዳለበትም ነው የጠቆሙት።
በሰለሞን ሰንታየሁ
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይሁኑ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን !

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here