ገጠር ተወልዶ ላደገ ሠው ወፍ ጥበቃ እና እረኝነትን የመሰሉ ውብ ዓለሞች መቼም ከትዝታ ማኅደር አይጠፉም።
በተለይ በዚህ ወቅት በተለይ በቆላማ አካባቢዎች አዝመራው ማሸት ይጀምሯል። ወጣቶች ከአዝመራው መካከል ከፍ ተደርጋ ከተሠራች ማማ ላይ ኾነው የደረሰውን አዝመራ ይጠብቃሉ። ዙሪያ ገባው አረንጓዴ ነውና መንፈስን ያድሳል። የአበቦች ፍካት ሀሴትን ያጎናጽፋል።
ወቅቱ የሚያማምሩ አበቦች የፈኩበት፣ እሸቱ የተንዠረገገበት፣ ደስ ከሚያሰኙ ነገሮች ባለፈ በማታው ብርድ፣ በሌሊቱ ቁር እና በማለዳው ውርጭ ይታወሳል። ይህንኑ ለማውሳት ይመስላል ቀደምቶቻችን ሲተርኩ “በጥቅምት አንድ አጥንት” የሚሉት። ሌላ ጊዜ ደግሞ በጥቅምት እኩሌታ አንድ ኩታም ተብሎ ይተረካል።
ከብርድ ጋር እየታገለ ወደ ማማው ለሚወጣ ማሽላ ጠባቂ በአገልግል የተቋጠረው ምግብ ጥፍጥናው ሌላ ነው። ንፍሮ እና ቆሎው ቢቀዘቅዝም ከልቡ ላፈቀረ መተከዣ ይኾናል። ከማማ ላይ ወጥቶ ወፍ የሚጠብቅ ጎረምሳ የወንጭፉን ድምጽ እንደ ሙዚቃ መሣሪያ ተጠቅሞ ከራሱ ጋር ያወጋበታል። የዋሽንቱን ዜማ ሲያንቆረቁረው ደግሞ ተፈጥሮ ነፍስ ዘርታ ከእሱ ጋር ትወዛወዛለች።
ማማ ላይ ወጥቶ ወፍ የሚጠብቅ ጎረምሳ እንደሱው ወፍ ከምትጠብቅ ኮረዳ ጋር ባሻጋሪ የፍቅር ስሜቱን የሚገልጽበት ምቹ አጋጣሚም ነው። በዓይን ፍቅር መለከፉን ስንኝ ቋጥሮ እና በዜማ ከሽኖ ከማማው ላይ ኾኖ ያንጎራጉርላታል።
“በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” እንዲሉ ወዲህ ማሽላው እየተጠበቀ፤ ወዲያ ደግሞ ፍቅር እየተወረወረ የሚዋልበት አዝመራ ጥበቃ ልዩ ትዝታ አለው። ለዚያም ይመስላል ድምጻዊ ኤልያስ ተባባል
“ከረጅም ማማ ላይ ጥንቅሽ የበላ ሠው፣
ከጎድጓዳ ሥፍራ ጠይም የሳመ ሰው፣
እንኳን ሽማግሌ ዳኛም አይመልሰው።” በማለት ያዜመው።
በሰፊው አዝመራ መካከል ከፍ ብላ የቆመች ማማ ከወፍ ጥበቃ የተሻገረ ታሪክ አላት። ስለ ፍቅር ይዜምባታል። ቅኔ ይቋጠርባታል። የወንጭፉ እና የዋሽንቱ ድምጽ፣ ፉጨቱ እና የማዶ ለማዶ የፍቅር ጨዋታው በትዝታ ማኅደር የሚቀመጥ ውብ ትዝታ ነው።
ለወፍ ጥበቃ በማለዳው ከማማ ላይ የወጣች ኮረዳ ይመጣል ብላ ተስፋ የጣለችበት ወጣት ቢዘገይባት ጊዜ
ከማማው ላይ ኾኜ ብጠቅሰው ብጠቅሰው፣ ምነው ድምጹ ጠፋ ይመጣል ያልኩት ሰው።
አንገቱ ‘ሚመስለው የጃምዮ መቃ፣
የት አገኘዋለሁ ብታጨድ ብወቃ።
ሰው ሁሉ አዝመራውን እያጨደ ወቃ፣
ምነው ዘገየብኝ የ’ኔ ወፍ ጥበቃ፤ በማለት ታንጎራጉራለች።
ወፍ በሚያረግፍ ሀገርኛ ለዛ የሚንቆረቆረውን የኮረዳዋን ተስረቅራቂ ድምጽ የሰማው ጎረምሳ ጎፈሬውን ነቅሶ እያፏጨ የመልስ ስንኝ ይቋጥራል።
ወፍ እጠብቃለሁ ዋርዳና የለል፣
ወገቧ ቀጭን ነው የኔ ጠንበለል።
የጥንቅሽ አገዳ መጥጬ ላምጥጥሽ፣
የሠው ስጋ እርም ነው ጨርሼ እንዳልውጥሽ።
ከማሽላ መሐል ይዘራል ሀዋዬ፣
ስጠራሽ ወይ በይኝ ማሬ ወለላዬ። በማለት በፍቅሯ መረታቱን ስንኝ ቋጥሮ በዜማ ይመልስላታል።
እንደየ አካባቢው ወቅቱ ቢለያይም የወፍ ጥበቃ እና የማማ ላይ ጨዋታ የሚናፈቁ አንዳንዴም ተመልሰው የማይገኙ አይረሴ ትዝታዎች አሉት። ከወፍ ጥበቃው ጎን ለጎን በምትወደው ልጅ የዓይን ፍቅር የተለከፈች ሳዱላ የውስጧን የምትተነፍስበት አጋጣሚም ታገኛለች።
አሞራ ይበራል ሠማይ ለሠማይ፣
ወፎቹ እህል ፈጁ አንተን አንተን ሳይ።
ማሽላ ጠባቂ ይውላል ከማማ፣
ዓይንህና ዓይኔ ነው ነገረኛውማ።
አንተ ወዲያ ማዶ ወፍ ትጠብቃለ፣
እኔ ወዲህ ማዶ ወፍ አጠብቃለሁ፣
አንገትዋ ሸጌ ከማማው ላይ ውረድ እሞትብሀለሁ። በማለት ትጫወታለች በውብ ዜማ።
ኮበሌውም በፊናው፦
ሽምብራ በሸቱ ጤፍ በወለዳው፣
እንዳንች እና እንደኔ የኾነው ማነው።
የአምባሠል ማር እሸት የየጁ ጥንቅሽ፣
ፍቅርሽ የሚጣፍጥ አድሮ ‘ሚያገረ።
ማሽላ ዘርቼ ጥንቅሽ አልዘራሁም፣
አንችን የሚያስረሳ ሰው አላገኘሁም። በማለት በፉጨት አጅቦ ነጻነት በተሞላበት ቃና ፍቅሩን ይገልጽላታል።
የማማ ላይ ጨዋታ እና የወፍ ጥበቃ፣ ፍቅር እና አብሮነት መዋደድ እና ኢትዮጵያዊነት የሚታይበት ውብ ትዝታ ነው።
በፍቅር የተረቱ ልቦች እንደ ከተሜ ሰው በየመዝናኛው ቁጭ ብለው የሚያወጉበት አጋጣሚው የላቸውምና ስንኝ ቋጥረው እና በዜማ ከሽነው የሚተነፍሱበት የጥበብ መድረክም ነው-ማማ።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ደሴ #ጥቅምት_07_2019_ዓ_ም
✍️ ጀማል ይማም
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









