የዓለም ድንቅ የቱሪስት መዳረሻ የኾነችው ላሊበላ ከተማ የዘመናት የቱሪስት መናኸሪያነቷን እና ውበቷን ይዛ እንግዶቿን በናፍቆት ለመቀበል ሽርጉድ ማለት የዘወትር ተግባሯ ነው።
ከኮቪድ ወረርሽኝ ጀምሮ ባለፉት ዓመታት በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት ቱሪዝሟ ሲቀዛቀዝ ተስተውሎ ነበር። ዛሬ ላሊበላ ከተማ ያ ሁሉ ጊዚያት አልፈው በአንጻራዊ የሰላም ብርሃን እየታደሰች ትገኛለች።
የላሊበላ ሎጅ ባለቤት እና የከተማዋ ሆቴሎች ማኅበር አባል የሆኑት አቶ ሀብታሙ ከባዱ “ሰላም እና ቱሪዝም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ይላሉ በሰላም ወራት የነበረውን ያንን የድምቀት ጊዜ እና የገቢ ማማ በናፍቆት እያስታወሱ። በላሊበላ እና አካባቢው አሁን ላይ ሰላም እና መረጋጋት እንዳለም ገልጸዋል።
የላሊበላ ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ መሳይ ወዳጄ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በላሊበላ ከተማ እና አካባቢው ፍጹም ሰላም ነው ብለዋል። “ሰላማችን አስተማማኝ ነው” በማለት የከተማዋን አሁናዊ የሰላም ሁኔታም አረጋግጠዋል።
ባለፈው ዓመት ከ9 ሺህ በላይ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን በመቀበል ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ከንቲባው አስታውሰዋል። ከጎብኝዎች ውስጥም ከ3 ሺህ በላይ የሚኾኑት የውጭ ቱሪስቶች ናቸው ብለዋል።
በዚህ ዓመትም ከባለፈው ዓመት የተሻለ ቱሪስቶች እንዲመጡ እና የተሻለ ገቢ ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው፤ ለዚህም በአካባቢው አስተማማኝ የጸጥታ ሁኔታ ተፈጥሯል ነው ያሉት። በቂ እና ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እና ሬስቶራንቶችም ተዘጋጅተዋል። በከተማዋ የ24 ስዓት የኢንተርኔት እና የመብራት አገልግሎት መኖሩንም ከንቲባው ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!









