ዲማ ጊዮርጊስ፡- ከፍቅር እስከ መቃብር መቼትነት ባሻገር !

0
23
የሃይማኖት እና የጽናት ዓምድ፣ የዘመናት ታሪክ ማኅደር የኾነው የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም መሠረቱ የተጣለው በአጼ አምደ ጽዮን ዘመነ መንግሥት ነው።
በምሥራቅ ጎጃም ዞን በእነማይ ወረዳ ከብቸና ከተማ ጥግ የሚገኘው ይኸው ሥፍራ በአባ በኪሞስ (ተከስተ ብርሃን) ነው የተመሠረተው። በአጼ ይስሐቅ ዘመን የተጠናከረው ገዳሙ የሊቃውንት መኖሪያ እና የመንፈሳዊ ዕውቀት ማዕከል ኾኖ ዘልቋል።
🎯 የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም:-
👉 የአጼ ዮሐንስ አራተኛን የወርቅ ዘውድ እና መስቀል፣
👉 የአጼ ይስሐቅን የወርቅ ጫማ፣
👉 የወርቅ በትረ ሙሴ፣
👉 የአርባአቱ ወንጌላውያን እና የገድለ ጊዮርጊስ መጻሕፍት፣
👉 የንጉሥ ተክለሃይማኖት ጦር፣
👉 የራስ መኮንን ካባ እና ሌሎች ውድ ምስጢራዊ ቅርሶችን በታሪካዊ ግምጃ ቤቱ ይዟል። የታሪክ መዘክር የኾነው የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም በዘመኑ ትውልድ የሚታወቀው በፍቅር እስከ መቃብር መቼትነቱ ብቻ ነው። ገዳሙ ከዚህ ባሻገር የዕውቀት፣ የጽናት እና የብራና ባለቤት መኾኑ ሲዘነጋ የታሪክ ዕንባው ትውልዱን በጸጥታ ይወቅሰዋል።
በመላ ኢትዮጵያውያን በፍቅር እስከ መቃብር የታወቀውን የዲማ ጊዮርጊስ ገዳም ከምናብ ባሻገር በአካል ለማሳየት እና ለዕንቁ ቅርሶቹ ማረፊያ ሙዚየም እየተገነባ ነው።
የእነማይ ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት የቅርጽ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ ደስታ ገብረመድህን እንደገለጹት ይኸው የሙዚየም ግንባታ 95 በመቶ ላይ ደርሷል። ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የኾነበት ሙዚየሙ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የሚኾነው ከኅብረተሰቡ የተገኘ ነው። ይህም ትውልዱ በታሪክ ብቻ የሚኖር ሳይኾን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ መነሳቱን የሚያሳይ ነው።
ሙዚየሙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለጎብኚዎች ክፍት በማድረግ፣ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ በማድረግ እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን ከቅርስ ጥበቃ ጋር ለማስተሳሰር ያለመ ነው።
የሕንፃው ዙሪያ እና የኤሌክትሪክ ሥራዎች የተጠናቀቁ ቢኾንም የውስጥ መደርደሪያዎች፣ ዲጂታል ካሜራዎች እና ለጥንታዊ የግድግዳ ስዕሎች ጥገና አሁንም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ የፍቅር እስከ መቃብርን ዘላለማዊ ትርክት ከታሪካዊ አሻራዎች እና ውድ ቅርሶች ጋር ለማስተሳሰር የዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳምን መጎብኘት የመጽሐፉ አንባቢያን ታሪካዊ ኀላፊነት ነው።
✍️ዘጋቢ:-ስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here