የጎጃሙ ጣሪያ፤ ጮቄ ተራራ

0
38
🇪🇹
ከባሕር ወለል በላይ እስከ 4 ሺህ 100 ሜትር ከፍታ የሚገኘው ጮቄ ተራራ፤ በአማራ ክልል ቀልብን ከሚገዙ ድንቅ ተፈጥሯዊ መልክዓ ምድሮች መካከል አንዱ ነው። ቀዝቃዛ አየሩ መንፈስን በአዲስ ሕይወት የሚያላብስ፣ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ በአጓጊ ውበቱ የሚማርክ ድንቅ
ስፍራ ነው። ይህ ግርማ ሞገስን የተላበሰ ተራራ አረንጓዴ የደን ክምችትን ለብሶ ማየት ለዓይን ማራኪ፣ ለአዕምሮም እረፍት የሚሰጥ ሕያው ስዕል ነው። በለምለም አቃፊነቱ የሚታወቀው ይህ የተፈጥሮ ሀብት ከሰባት በላይ ወረዳዎችን አቅፎ የያዘ እጅግ ሰፊ እና ድንቅ ሥነ-ምሕዳር ነው።
ከአረንጓዴው ዳገት እስከ ቁልቁለቱ ድረስ የሚንቆረቆሩት ከ270 በላይ ምንጮች እና ከ59 በላይ ታላላቅ ወንዞችም ይፈስሱበታል። በተራራው ግርማ ሞገስ በተሞላው አረንጓዴ መጎናጸፊያ ውስጥ ነብር፣ ቀበሮ፣ ጉሬዛ፣ ድኩላ እና ሌሎችም አጥቢ እንስሳት ከበርካታ ሀገር በቀል እጽዋት ጋር
ተጣምረው ይኖሩበታል። ይህ ውብ ስፍራ ለተፈጥሮ ወዳጆች እና ለጎብኝዎች ማራኪ መዳረሻም ነው። በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የጮቄ ምርምር እና ልማት ዳይሬክተሩ አማረ ተስፋው (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ከ15 ዓመታት ወዲህ ይህንን የተፈጥሮ ሀብት ከጥፋት ለመታደግ ሰፊ የምርምር
እና የጥበቃ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ዛፎችን እና ቁጥቋጦዎችን ከጉዳት የመጠበቅ ሥራም እየተከናወነ ነው ብለዋል። የአፈር መሸርሸር መከላከያ ሥራዎችን በማጠናከር የተራራውን ደን እና ውኃ የማቆየት አቅም ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት።
የድኅረ ምረቃ ተማሪዎችን በጮቄ ሥነ ምሕዳር በማሠማራት ሰፊ ሳይንሳዊ ጥናቶችን በማካሄድ ረገድ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋልም ብለዋል። የሰዎች እና የእንስሳት ጫና በሰፊው በሚታይባቸው አካባቢዎች የአርሶ አደሮችን አኗኗር ከዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ጋር በማቀናጀት እና
የማኅበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለቀጣይ ሥራዎች ቁልፍ መፍትሔ ኾኖ ተቀምጧል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። በተጨማሪም ቦታው የኢኮ-ቱሪዝም መዳረሻ እንዲኾን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኔስኮ እንዲመዝገብ እየተሠራ እንደሚገኝ ዶክተር አማረ ገልጸዋል።
✍️ በሕይወት አሸብር (ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በአሚኮ የተግባር ተማሪ)
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here